ልዩ ልዩ

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዘመን የሚቆጠርበት ቀመር የሚቀመርበት ትምህርት ባሕረ ሐሳብ ይባላል። ባሕረ ሐሳብ ከሁለት የግእዝ ቃላት የተገኘ ነዉ። ባሕር ማለት በዘይቤ ሳይሆን በምስጢር ወይም በምሳሌው ዘመን ማለትን ያሰማል። በመዳልው ደለወ ዓለመ ወበመስፈርት ሰፈራ ለባሕር እንዲል። ባሕርን ሰፈራት ይላል ባሕ የሚሰፈር ሳይሆን ባሕርን ዘመን ለማለትና ዘመን በአዕዋዳት የሚታወድ በቀመር የሚቀመር የሚሰፈር መሆኑን ለማሳየት ነዉ። ሐሳብ ማለት ፍቺው ብዙ ቢሆንም እዚህ ላይ በአጭሩ ቁጥር ማለት ነው። ኢትትሐሰብዎሙ ወርቆሙ ወብሩሮሙ ወለጽድቅከኒ አልቦቱ ሐሳብ - ለቸርነትህ ቁጥር ሥፍር የለውምእንዲል አረጋዊ መንፈሳዊ እንዲሁም ቅዱስ ዳዊት ብፁዓን እለተኀድገ ሎሙ ኀጢአቶሙ ወእለኢሐሰበ ሎሙ ኩሎ ጌጋ - ኀጢአታቸዉ የተተወላቸው በደላቸው ያልተቆጠረባቸው ብፁዓን ናቸው መዝ 311 ይላል። ስለዚህ ባሕረ ሐሳብ ማለት የዘመን አቆጣጠር ማለት ይሆናል። ሐሳበ ባሕርም ቢል ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው።
ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠራችን የበዓላትና የአጽዋማት አከባበራችን የሚመነጨው ባሕረ ሐሳብ ነው። አንድ ዘመን በውስጡ 13 ወራት ወይም 365 1/4 /ከሩብ/ ቀናት ያሉት ሲሆን ይህ አንድ ዘመን /ዓመት/ አራት ክፍላ ዘመናት አሉት። እነዚህም
1. መፀው /መኸር/ በዚህ ወቅት ተዘርቶ የከረመው አዝርዕት ለዘር የሚበቃበት ሰማያት በከዋክብት ምድርም በሥነ ጽጌያት የሚያሸበርቁበት ወቅት ነው። ዘከለልኮ ለሰማይ በከዋክብት ወለምድኒ በሥነ ጽጌያት እንዲል ቅዱስ ያሬድ።
2. ሐጋይ /በጋ/ ምድር በፀሐይ ሐሩር የምትቃጠልበት ልምላሜ የሚጠፋበት አታክልቱ በአቧራ የሚሸፈኑበት ምንም ዝናም የሌለበት ወቅት ነው።
3. ፀደይ /በልግ/ በዚህ ወቅት ምድር ትንሽ ዝናም የምታገኝበት በተወሰነ ደረጃ ልምላሜ የሚታይበት ወቅት ነው።
4. ክረምት ከረመ ማለት ሲሆን ምድር በዝናም የምትቆይበት ጊዜ ነው።
የኢትዮጵያ ዐዲስ ዘመንም የሚገኘው ከዚህ ከዘመነ ክረምት ውስጥ ሲሆን ይህ ዘመነ ክረምት በራሱ ሰባት ክፍላት አሉት። እነዚህም
1. ከሠኔ 26 እስከ ሐምሌ 19 ድረስ ያሉት 23 ዕለታት ክረምት ወይም የዘር ወቅት ይባላል። በዚህ ወቅት ዝናም የሚጀምርበት ምድርም በሚወርደው ዝናም የምትረሰርስበት ጊዜ ነው። ቅዱስ ዳዊት ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር - ሰማያትን በደመና የሚሸፍን ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ /የፈጠረ/ እርሱ እግዚአብሔር ነው።መዝ 14615 በማለት ስለዚሁ ወቅት ተናግሯል። በዚህ ወቅት ገበሬው በዝናም የራሰውን ምድር አይሞ፣ አለስልሶ ዘር የሚዘራበት ጊዜ ነው። ቅዱስ ያሬድም ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ያን ይፀግቡ ርኁባንበማለት በዝናም አማካኝነት እንስሳቱም ሌሎች ፍጥረታት የሚደሰቱበት፣ የሚጠግቡበት ጊዜ መሆኑን በድርሰቱ ገልጾታል።
2. ከሐምሌ 20 እስከ ነሐሴ 10 ያሉ 21 ዕለታት ምልአተ ባሕር - የባሕር መሙላት ይባላል። በዚህ ወቅት የዝናሙ መጠን ጨምሮ ከየተራራዎቹ የሚወርደው ዝናም በባሕር ውስጥ ተሰብስቦ የሚሞላበት ወቅት ሆኖ በዚህ ወቅት የባሕር መሙላት ብቻ ሳይሆን ሳት ደመናት፣ ነጐድጓድና መባርቅት የሚታሰቡበት ነው። የሚሰበከው ምስባክ የሚሰጠውም ትምህርት ሆነ የሚደርሰው ዝማሬና ምስጋና እነዚህን ሁሉ የሚያወሳ ነው።ባሕርኒ ርዕየቶ ወአዕኩተቶ ምድርኒ ገደት ሎቱ - ባሕር አየች አመሰገነች ምድርም ለእርሱ ሰገደችለትይላል ቅዱስ ያሬድ።
3. ከነሐሴ 11 እስከ 27 ድረስ ያሉ 17 ዕለታት ደግሞ ዕጉለ ቋዓት፣ ደሰያት ዐይነ ኩሉ ይባላል። ዕጉለ ቋዓት - የቁራ ልጅ ማለት ሲሆን ቁራ ገጽታው ልጅን ስትወልድ ጫጩቷን ስትፈለፍል እንደሌሎች ፍጥረታት ራሷን የሚመስል ሳይሆን ከርሷ የተለየ፣ ላባ (ፀጉር) የሌለው ነጭ /ቀይ/ ቆዳ ብቻ ያለው ነው። ጫጩቱ በመልኩ ከእርሷ ስለሚለይ የገዛ እናቱ ጫጩቱን ፈርታ ትሸሻለች በዚህ ጊዜ ጫጩቱ አሳደሪ ረጅ የለውም። ነገር ግን እግዚአብሔር በረቂቅ ጥበቡ የጫጩቱን አፍ እንዲከፈት አድርጐ በዝናቡ ምክንያት የሚፈጠሩ ጥቃቅን ፍጥረታት አፉ ዉስጥ ሲገቡ እነዚህን እየተመገበ ላባው(ፀጉር) አቆጥቁጦና አድጐ እናቱን ይመስላል። እናቱም እርሷን ስለመሰለ መፍራቷን ትታ ትቀርበዋለች። በዚህ የተነሣ ቋዓት- ቁራዎችን ያለ እናት እና ያለ አባት የሚመግብ እግዚአብሔር መግቦቱ የሚነገርበት ጊዜ ነው። ቅዱስ ዳዊት ዘይሁቦሙ ሲሳዮሙ ለእንስሳ፣ ወለእጉለ ቋዓት እለ ይጼውዕዎ - ለእንስሶችና ለሚጠሩት ለቁራዎች ጫጩቶች ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ ነው።መዝ 1469 ይላል። ዳግመኛም ዐይነ ሁሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ - የሁሉም ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋልእንዳለው ፍጥረታት ሁሉ በእግዚአብሔር ቸርነት ተስፋ አድርገው እንደሚኖሩ የሚታሰብበት ወቅት ነው።
ደሰያት - ደሴቶች ሲሆኑ ዙሪያቸው በውሃ የተከበበ የየብስ ክፍሎች ናቸው። እነዚህ ደሴቶች በምልአተ ባሕር ምክንያት ውሃው ሳይደርስባቸው ባሉበት ሁኔታ ተጠብቀው ባሕርም ከዐቅሟ በላይ ሳትዘል ባለችበት ስለምትጸና እነዚህ ደሰያትም ሚዘከሩበት ወቅት ነው። ደሴቶችም ደስ ይበላቸውመዝ 962
4. ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜ 5 ድረስ ያሉት 7 ዕለታት ጎሐ ጽባሕ፣ ነግህ፣ ብርሃን መዓልት ይባላል። በዚህ ወቅት የክረምቱ ዝናም ቀንሶ ምድርን ሸፍኗት የከረመው ደመና የሚገፈፍበት፣ ብርሃን የሚፈነጥቅበት ወቅት ስለሆነ ጎሐ ጽባሐ ይባላል። ቅዱስ ያሬድ ጎሐ ጽባሕ ዘአንተ ሠራህከ - የጠዋትን ውጋገን የሠራኸው አንተ ነህበማለት ጨለማውን ዘመን በብርሃን የሚተካ እግዚአብሔር መሆኑን በድርሰቱ ገልጾታል።
5. ከመስከረም 1 እስከ 8 ያሉ ዕለታት ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል። ይህ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የሚጀመርበት ዐዲስ ዘመን ነው።  ይህ ጊዜ ርእሰ ዐውደ ዓመት የሚባልበትና ቅዱስ ዮሐንስም የርእሰ ዐውደ ዓመቱ መጠሪያ እንዲሆን አባቶቻችን በደነገጉት መሠረት መጥምቁ ዮሐንስ የተሰየመበት ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የነቢያት ፍጻሜ፣ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ፣ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ በመሆኑ፣ እንዲሁም በመስከረም 2 ቀን በንጉሥ ሄሮድስ ትእዘዝ አንገቱ የተሰየፈበት በመሆኑ ርእሰ ዐውደ ዓመቱ በቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እንዲሰየም ተደርጓል።
6. ከመስከረም 9 እስከ 15 ያሉ 7 ዕለታትም ፍሬየሚባ ሲሆን የተዘራው ዘር ደርሶ ለፍሬ መብቃት የሚጀምርበት ጊዜ ነው። ገበሬው የዘራው ዘር ሁሉ ለፍሬ ባይበቃም አብዛኛውን 30 60 100 ፍሬዎችን አፍርቶ እሸት መብላት የሚጀመርበት ወቅት ስለሆነና ገበሬው ያሳለፈው ውጣ ውረድና ድካም ከንቱ ሳይቀር ለፍሬ የሚበቃበት ወቅት ስለሆነ ዘሩንም ከተለያየ አደጋ አትርፎ ለፍሬ ያበቃው አምላክ የሚመሰገንበት ጊዜ ነው። ቅዱስ ዳዊትወሶበ የአትዉ መጽኡ አንዘ ይተፌሥሑ ወፆሩ ላስቲሆሙ - በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉእንዳለ መዝ 1256
7ከመስከረም 17 እስከ መስከረም 25 ድረስ ያሉ 9 ዕለታት መስቀል የሚባ ሲሆን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በአይሁድ ምቀኝነት ተቀብሮ ከቆየ በኋላ በንግሥት እሌኒ አማካኝነት ፍለጋ የተደረገበትና ቁፋሮ የተጀመረበት መስቀሉ ከወጣ ኋላም ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ የተከበረበት ጊዜ ስለሆነ መስቀልይባላል።
                                      
ብቸኛውና ትክክለኛው የዘመን አቆጣጠር
          በዓለም ላይ በርካታ የዘመን አቆጣጠሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል የጎርጎርዮስ የዘመን አቆጣጠር ዲሜጥሮሳዊ የዘመን አቆጣጠር የጁሊየስ ቄሳር፣ የዐረብ፣ የአይሁድ... ወዘተ የዘመን አቆጣጠሮች አሉ። ከእነዚህ የዘመን አቆጣጠሮች በተጨማሪ ብቸኛና ልዩ የሆነ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር አለ። የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከሌሎች የዘመን አቆጣጠር በተለይም በዓለም ላይ በስፋት ከሚታወቀው የአውሮፓውያን / የጎርጎርዮሳውያን/ የዘመን አቆጣጠር በበርካታ ነገሮች ይለያል። ለአብነት ያህል

1. የዘመን መለወጫ በመስከረም መሆኑ፡
          አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠራቸውን የሚጀምሩት በጥር ሲሆን ኢትዮጵያውያን ግን ዘመናችንን ምንለውጠው በመስከረም ነው ለዚህም በርካታ የሆኑ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ ትውፊታዊ ምክንያቶች አሉ። ሃይማኖታዊ  ምክንያቶች መካከል በዘፍ 88 ላይ እንደተገለጸው ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውሃ ድነው ከመርከብ ወጥተው በምድር ላይ አርፈዋል። ይህንም ቀን በየዓመቱ ያከብሩት ነበር። በመጀመሪያ ወር መባቻ ለራሱ መርከብ ይሰራ ዘንድ ታዘዘ በእርሷም ምድር ደረቀችኩፋ 724 ስለዚህ ምድር የደረቀችው በመጀመሪያ ወር መባቻ /መግቢያ/ በመሆኑ ይህን በየዓመቱ ያከብሩታል። ኖኅ ልጅ ከነዓን፣ ልጆቹ አቢስና ኩሽ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ይህን በዓል በየዓመቱ ያከብሩት ነበር። ይህም ቀን መስከረም አንድ ቀን ነው። በዚህም ቀን እስራኤላውያን ዘመናቸውን እንዲለውጡ እግዚአብሔር ሙሴ አዞታል ዘሌ 2335 ይህም ቀን የዘመን መለወጫ ሆኖ በትውፊት /በቅብብሎሽ ወይም በመወራረስ/ ከእኛ ዘመን ደርሷል። ሌላው ምክንያት የክረምቱ ዝናም የሚያቆምበት፣ ጨለማ የሚወገድበት ጉምና ደመና የሚሰበሰቡበት በምትኩ ጎሕ የሚቀድበት፣ የብርሃን ጮራ የሚፈነጥቅበት በመሆኑ ዘመናችንን መስከረም አንድ እንለውጣለን።

2. የሰባት ዓመት ከስምንት ወር ልዩነት መኖሩ
አውሮፓውያን ከእኛ የዘመን አቆጣጠር ሰባት ዓመት ከስምንት ወር ይቀድማሉ። በእኛ 2006 ሲሆን በእነርሱ 2013 ነው። ከአራት ወራት በኋላ 2014 ይሆናል። የዚህ ልዩነት ሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ነው። ለዚህ ልዩነት የሚሰጠው ምክንያት አንዳንዶች ኢትዮጵያውያ የክርስቶስን ልደት ዘግይተን የሰማን መሆናችንን ሲናገሩ አንዳንዶች ደግሞ አዳም በገነት የቆየበትን ሰባት ዓመታት የማንቆጥር መሆኑንና ሌሎችም መላምቶች ይሰነዝራሉ። ነገር ግን ሁሉም መላምቶች ትክክል አይደሉም። ኢትዮጵያውያን የክርስቶስን ልደት ከማወቅ አልፎ ቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበረው ባዚን በቤተልሔም ተገኝቶ አምኃ /ስጦታ/ ካቀረቡት ነገስታት አንዱ ነበር እንዲሁም አዳም በገነት የቆየበትን ሰባት ዓመትም ቢሆን ጠንቅቀን ስለምናውቅ እኛ ኢትዮጵያውያን ከዓመተ ዓለም ጋር አብረን እንቆጥረዋለን።
ከጌታችን ልደት በፊት የነበረዉ 5500 ዓመተ  ዓለም ውስጥ ይህ ሰባት ዓመት ዐብሮ ተካቷል። ምክንያቱም "በኀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ - ዐምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም አድንሃለሁ" /ቀሌምንጦስ/ የሚለዉ የተስፋ ቃል ተቀብለናል። ይህ ዐምስት ሺህ ዐምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ማለት ነዉ። በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከቆጠረ ዐምስት ሺኽ ዐምስ መቶ ዘመን ሲፈፀም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዷል። ስለዚህ ትክክለኛው የዘመን አቆጣጠር በእርግጥም የኢትዮጵያ ነው።

3ኛ/ 13ኛ ወር መኖሩ:
          አውሮፓውያን ወራቶቻቸው ዐሥራ ሁለት ሲሆን ወራቱ ወጥነት የሌላቸው 31፣30፣28 ቀናት ያሏቸው ወራቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ግን ባለሙሉ 30 ቀናት 12 ወራትና ዐምስት ወይም በአራት ዓመት አንዽ ጊዜ ስድስት ቀናት ያሏት 13ኛ ወር ያላት ናት። ይህ የሆነበት በኢትዮጵያ ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት መሆኑ ሲሆን በአውሮፓውያን ግን ቀኑና ሌሊቱ በየጊዜው ይቀያየራል።
          ጳጉሜን በአራት ዓመት ስድስት የምትሆነው አንድ ዓመት የሚባለው 365ቀናት ከ15 ኬክሮስ /ከስድስት ሰዓት/ ነው። ስለዚህ ይህ 15 ኬክሮስ ወይም የቀን 1/4ኛው በአራት ዓመት ሙሉ ቀን ስለሚሆን ይህ በአራት  ዓመት በዘመነ ሉቃስ ላይ ተጨምሮ ጳጉሜን ስድስት እንድትሆን ያደርጋታል። ጳጉሜን ማለትም ተውሳክ፣ ጭማሪ፣ ተረፍ ማለት ነው።

4ኛ. ዘመናቱ በወንጌላዉያን መሰየማቸው:
          በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እያንዳዱ ዘመን በወንጌላውያን የተሰየመ የተጠራ ነው። የጌታችን የመድኀኒታችንን ቅዱስ ወንጌል የጻፉት አራት ወንጌላውያን ናቸው። ወንጌል ማለት የምሥራች ማለት ሲሆን በምዽር ላይ ነግሦ የነበረው ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተወግዶ  ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ መደረጉ፣ የሰው ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን መሸጋገሩ፣ ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነጻ መውጣቱ የተገረው በወንጌል ነው። ይህችን ደገኛይቱ ሕግ የተባለችውን ወንጌልን አራቱ ወንጌላውያን በተለያየ ጊዜ፣ በተለያየ ቦታ ሆነው ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በምስጢር ሳይለያዩ ጽፈው ለእኛ አበርክተዋል። ለዚህ ውለታቸው የቀደሙት ቅዱሳን አባቶቻችን በየምሳሌ ነገራቸው ዘመናት በስማቸው እንዲሰየም ደንግገዋ።
የዘመኑን ወንጌላዊ ለማወቅ 5500 ዓ.ዓ ና ዓመተ ምሕረት ደምረን ለአራት በማካፈል ቀሪው 1 ከሆነ ማቴዎስ፣ 2 ከሆነ ማርቆስ፣ 3 ከሆነ ሉቃስ፣ አልቦ /ዜሮ/ ከሆነ ዮሐንስ ነው።
ለምሳሌ የ2006 ዓ.ም ወንጌላዊውን ለማወቅ
                5500 ዓ.ዓ + 2006 ዓ.ም = 7506 ዓ.ዓ
                7506 ÷ 4 = 1876 ጊዜ ደርሶ ቀሪው ሁለት ይሆናል
                ስለዚህ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ ነው።
 
5ኛ. የዐሥር ቀናት ልዩነት
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር መስከረም አንድ ቀን ሲሆን በአዉሮፓውያን ግን መስከረም ዐስራ አንድ ቀን ይሆናል። ለዚህም የ10 ቀን ልዩነት አለ። ይህም የሆነው በ1582 ዓ.ም የካቶሊክ 13ኛ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ፖፕ ጎርጎርዮስ በፊት ይቆጠርበት የነበረውን አንድ ዓመት 365 ቀን ከ6 ሰዓት የሚለውን ቀይሮ 365 ቀን ከ5 ሰዓት እንዲሆን ወስኗል። በዚህም የተነሣ በዓመት አንድ ሰዓት የተጨመረውን ከጉባኤ ኒቂያ ጀምሮ በመደመር ወደ ቀን ለውጦ ዐሥር ቀን አድርሶታል። በዚህም ጥቅምት 5 ቀን የነበረውን  ጥቅምት 15 እንዲሆን በማወጁ የ10 ቀን ልዩነት ሊፈጠር ችሏል።  የኢትዮጵያ ቤ/ክ ግን ዓመቱ 365 ቀን ከ15 ኬክርስ /ከስድስት ሰዓት/ ነው በማለት ይህንን የቀን ጭማሪ አትቀበለውም።
ከላይ እንደተመለከተው ዐዲስ ዘመን የሚጀምረው መስከረም አንድ ቀን ሆኖ ይኼም በባሕረ ሐሳብ ዕለተ ቀመር ይባላል። ለኢትዮጵያዊያን ቁጥር የምንጀምርበት ስለሆነ ዕለተ ቀመር ተብሏል። በዚህ ወቅት በደመና የተሸፈነው ምድር በጎሕ የሚተካበት፣ ብርሃን የሚፈነጥቅበት፣ ምድር አረንጓዴ ለብሳ ልምላሜዋ የሚታይበት የአትክልቱ መዐዛ የሚያውድበት ወቅት ነው።
በዚህም የተነሳ የሰው አእምሮ ይታደሳል ይደሰታል። በዐዲስ መንፈስም ለሥራ የሚነሣሣበት ወቅት ነው። ቅዱስ ጴጥርስ በ1ኛ ጴጥ=ምዕ 4÷3 ላይ "ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል"  የሚል ኀይለ ቃል አስቀምጧል። ከዚህ ኀይለ ቃል በርካታ ነገሮችን የምንማርበት ነው። ዐዲስ ዘመን ሲመጣ በዓል አክብሮ፣ ዘመኑን ቆጥሮ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ካለፈው ዘመን የምንማራቸው ነገሮችን ለይተን ማስቀመጥና ጥሩ ሠርተን ያለፍነውን የምናጠናክርበት ያጐደልነውና የደከምንበት ላይ ደግሞ የምናሻሽልበት፣ የምንለውጥበትን መንገድ የምንቀይስበት ጊዜ ነው። በተለይም በዐዲስ ዘመን "በዘኃለፈ ስርየት ወለዘይመጽእ ዕቅብት- ያለፈውን ይቅር ይበለን በሚመጣዉ ይጠብቀን" የምንልበት የንሰሐ ጊዜ ሊሆን ይገባል:- ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳስተማረው "የአሕዛብን ፈቃድ የፈጸማችሁበት ማለትም ዝሙትና ምኞትን ስካርንና ወድቆ ማደርን ያለልክ መጠጣትና ጣዖት ማምለክን ያደረጋችሁበት ዘመን ይበቃችኋል" ባለው መሰረት ራሳችንን ለኀጢአት ያስገዛንበት ዘመን ከነበረ ለገቢረ ጽድቅ፣ በአምልኮተ ጣዖት የተያዝንበት ከነበረ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የምንመለስበት፣ ነፍሳችንንም ሆነ ሥጋችንን አንጽተን ራሳችንን የምንለውጥበት ሊሆን ይገባል። አለበለዚያ ዘመኑ በላያችን ላይ እየተፈራረቀና እየተቀየረ እኛ ግን በዚያ ቆመን በጠባይና በግብራችን የማንለወጥ ከሆነ ከንቱ ነው። ዘመኑ ሲለወጥ እኛም ዐብረን በንሰሐ እየታጠብን የምንለወጥበት ጊዜ መሆን ይገባዋል።
በአጠቃላይ ከላይ እንደተመለከተው ከሰባቱ የክረምት ክፍሎች ውስጥ አንዱ ጎሐ ጽባሕ ሲሆን በዚህ ጊዜ የክረምቱ ደመና ተወግዶ፣ ጨለማው ተገፎ በምትኩ ጎሕ የሚቀድበት ብርሃን የሚፈነጥቅበት፣  እንደሆነ ሁሉም እኛም በአሮጌው ዘመን በሕይወታችን ውስጥ ተጋርዶ የቆየውን ደመና፣ ተሸፋኖ የቆየውን ጨለማ አስወግደን ብሩህ ተስፋ የምንሰንቅበት፣ ዐዲስ አስተሳሰብ የምንይዝበትና ዐዲስ አዕቅድ አቅደን፣ የጐደለንን መሙላትና ድካማችንን በብርታት የምናርምበት ሊሆን ይገባል። ከዘመኑ ጋር አስተሳሰባችን አመለካከታችን ጭምር ዐብሮ መለወጥ አለበት።
ዐዲሱ ዘመን የሰላም የብልጽግና፣ ዐዳዲስ ነገሮችን አቅደን እነዚህንም በመፈጸም ራሳችንን ለንስሐ የምናዘጋጅበት፣ ለቤተክርስቲያናችን የቁርጥ ቀን ልጆች ሁነን አለኝታችንን የምናሳይበት፣ ወገኖቻችንን የምናስብበትና የምንረዳበት እንዲሆንልን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎትና በረከት አይለየን።

የ2006 ዓ.ም በዓላትና አጽዋማት

ወንበር -    0 (አልቦ)                  1 ጾመ - ነነዌ  የካቲት 3
አበቅቴ -    0 (አልቦ)                  2. ጾመ ኢየሱስ - /ዐብይ ጾም/ - የካቲት 17
መጥቅዕ -      30                      3. በዓለ - ደብረ ዘይት - መጋቢት 14
መባጃ ሐመር-  3                       4. በዓለ - ሆሳዕና - ሚያዚያ 5

የመስከረም አንድ ቀን፦                 5. በዓለ - ስቅለት - ሚያዚያ 10
ሌሊቱ /ሠርቀ ሌሊት/ - 2              6. በዓለ - ትንሣኤ - ሚያዚያ 12
ጨረቃ /ሠርቀ ወርኅ/ -  6              7. በዓለ - ርክበ ካህናት - ግንቦት 6
                                          8. በዓለ - ዕርገት - ግንቦት 21
                                          9. በዓለ - ጰራቅሊጦስ - ሰኔ  1
                                          10. ጾመ - ሐዋርያ - ሰኔ 2
                                          11. ጾመ - ድኅነት - ሰኔ 4 

አስርቆት
ሃሌ ሉያ በዘንዜከር ሐሳበተ ሕጉ ወትእዛዛቲሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኀኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሐሳበ ነቢያት ወሐዋርያት ሐሳበ ጻድቃን ወሰማዕታት፣ ሐሳበ ደናግል ወመነኮሳት፣ ሐሳበ ኄራን ወመላእክት እንዘ ሀሎነ በዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ዘመነ ማርቆስ ፍሰሐ ዜናዌ ሰብዓ ወሐምስተ ምእተ ወአርባዕተ ኮነ ዓመተ ዓለም ወእምኔሁሰ ሃምሳ ወሐምስተ ምእተ ኮነ ዓመተ ዓለም፣ ዓመተ ፍዳ ወዓመተ ኲነኔ፣ ዕሥራ ምእተ ወሰዱሰ ኮነ  ዓመተ ምሕረት ወዓመተ ሥጋዌ ዮም ሠረቀ ለነ ወርኀ መስከረም ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ወርኀ ጥምቀት በሰላመ እግዚአብሔር አብ አሜን።
ሠሉሱ ሠርቀ ሌሊት፣ አሚሩ ሠርቀ ዕለት ሰዱሱ ሠረቀ ወርኅ ረቡዑ ጥንተ ዕለት ሰኑዩ ጥንተ ቀመር አሚሩ ጥንተ ዮን ዮም በዛቲ ዕለት ዝ ጸሎት ይዕርግ በእንተ ስመ አብ በእንተ ስመ ወልድ በእንተ ስመ መንፈስ ቅዱስ በእንተ ስማ ለእግእዝትነ ወላዲተ አምላክ......እለ ዘከርነ ስሞሙ ወእለ ኢዘከርነ አስማቲሆሙ ዘበጽድቅ ይትወከፍ እግዚአብሔር። አሜን!
                                     
                                                                                             "ወስብሐት ለእግዚአብሔር"1 comment:

  1. I am sorry, but the world you using for this part doesn't sound appropriate. Can you please use another similar word?

    ReplyDelete

Thank you for your comments, we will response on timely manner.
thank you again.