ሥነ-ፍጥረት

 

በእንተ ዖፈ ብርጋና /ከርከዴዴን/

“ወሀለወት አሐቲ ዖፍ እንተ ስማ ከርከዴዴን እምዕለ ይሰርሩ በክንፍ  ዘትጸንስ በአሐዱ ወርኅ በሳልስ ወርኅ ወበሳድስ ወርኅ - በክንፋቸው ከሚበሩ ከርከዴዴን የምትባል ወፍ አለች። ይህችም በቀዳማይ ወርኅ /በመጀመሪያ ወር/፣ በሳልሳይ ወርኅ /በሶስተኛ ወር/፣ በሳድሳይ ወርኅ /በስድስተኛ ወር/ ትጸንሳለች። /መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘሐሙስ/

ከዕለተ ሐሙስ ሶስት ፍጥረታት መካከል አንዱ  በክንፋቸው ሚበሩ እንደሆነ ተመልክተናል። ከእነዚህ በክንፋቸው ከሚበሩ አዕዋፍ  መካከል ልዩ የሆነችና በመጽሐፈ አክሲማሮስ /የሥነ ፍጥረት መጽሐፍ/ ውስጥ በልዩ ሁኔታ ስሟና ተግባሯ ተዘግቦ የምናገኛት ወፍ አለች። የዚህች ወፍ ስሟ ከርከዴዴን ይባላል። በእርግጥ የዚህች ወፍ ሌላም መጠሪያ አላት። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የእመቤታችንን በድንግልና መጽነስና በድንግልና መውለድ በተናገረበት አንቀጹ ላይ ይችን ወፍ በምሳሌነት ያነሳት ሲሆን ስሟንም ሰደፍ ብሎ ጠርቷታል። /ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤፍሬም ገጽ 133/ አባቶቻችንም በግዕዙ ዖፈ ብርጋና ይሏታል። በዚህ ጽሑፍም ሆነ በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ስለዚህች ወፍ ከሌሎቹ ፍትረታት መካከል በልዩ ሁኔታ መዘገብ ያስፈለገው ለምንድ ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። የዚህ ምክንያቱ ይቺ ወፍ ያለዘር የምትጸንስ፣ ከዚህም አልፎ እንደሌሎቹ ፍጥረታት መሰሏን ማለትም ወፍ ብቻ ሳይሆን የምትወልደው እንቊ የምታስገኝ በመሆኗ ነው።                                                     ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ


እንቊ በዓለማችን ላይ ካሉ መድመቂያ ጌጣ ጌጦች መካከል የመጨረሻውና የከበረው  ነው። አንጥረኞች በሚያዘጋጁበት መንገድ ከሄድን አፈሩን ሰባት ጊዜ እንጥረው ብረት ይሆናል፤ ብረቱን ሰባት ጊዜ አንጥረው ብር ይሆናል፤ ብሩን ሰባት ጊዜ አንጥረው ወርቅ ይሆናል፤ ወርቁን ሰባት ጊዜ አንጥረው እን ቊ ይሆናል። ከእንቊ በላይ አይነጥርም። ምክንያቱም ዕንቊ ሁሉ የወጣለት ንጹሕ ጸሩይ ነው። እንግዲህ እንቊ ከሚገኝባቸው መንገዶች አንዱ ዖፈ ከርከዴዴን /ሰደፍ/ ከምታስገነው ነው።

ከላይ በመግቢያችን ላይ በጠቀስነው ጥቅስ ይህቺ ወፍ ሶስት ጊዜ የምትጸንስ ሲሆን በቀዳማይ ወር፣ በሶስተኛ ወር እና በስድስተኛ ወር ትጸንሳለች። የምትጸንሰውም ፀሐይ ስትወጣ ከባህር ወጥታ ሶስት ማዕረግ ከፍ ብላ የፀሐይ ግለት ባለበት ቦታ ጀርባዋን ለፀሐይ ሰጥታ ትመታለች። የፀህይ ብርሃን በደንብ አግኝታ ሰውነቷ /ገላዋ/ ሲቃጠል ረባ ወርዳ ከጥልቅ ባሕር ትገባለች። ረባ ወርዳ ከባህር ስትጠልቅ ከፀሀይ ጸዳል፣ ከውሃ ጠል ተከፍሎ በማኅጸኗ ይጸነሳል። በቅድሚያ በግራ ማኅጸኗ ሲሆን የምትጸንሰው በመጀመሪያ ሶስት አዕዋፍ ታስገኛለች። ቀትሎ አምስት አዕዋፍ፣ ከዚያም አስራ አምስት አዕዋፍ፣ ቀጥሎ አርባ ስድስት አዕዋፍ፣ በመጨረሻም ሰባ ሁለት አዕዋፍ ታስገኛለች። እነዚህ አዕዋፍ እስከ አርባ ቀን በእግራቸው ሲሽከረከሩ ቆይተው ከአርባ ቀን በኋላ በክንፋቸው ይበራሉ። በመቀጠል በቀኝ ማኅጸኗ እንቊውን ታስገኛለች። በመጀመሪያ አስራ ሁለት እንቊ ታስገናለች፤ ቀጥሎ ሰላሳ አምስት እንቊ፣ ከዚያም ሰባ ሁለት እንቊ፣ በመጨረሻም ክቡር እንቊ ታስገኛለች።

ይህ የበርካታ ነገሮች አምሳል ወይም ምሳሌ ነው። በመጀመሪያ ወር፣ በሶስተኛ ወር እና በስድስተኛ ወር መጽነሷ የሶስቱ ዘመናት ምሳሌ ሲሆን ይኸውም፦

·         የመጀመሪያ ወር … የዘመነ አበው /ከአዳም እስከ ሙሴ ያለው ዘመን/

·         የሶስተኛው ወር… የዘመነ ኦሪት /ከሙሴ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ /

·         የስድስተኛው ወር… የዘመነ ወንገል /ከኢየሱስ ክርስቶስ እስከ አሁን/ ያለው ዘመን ምሳሌ ነው።

ዖፈ ከርከዴዴን አዕዋፍ ከግራ ማኅጸኗ፣ እንቊ ከቀኝ ማኅጸኗ ያስገኘች ሲሆን ግራው የዘመነ ኦሪት ምሳሌ ነው። ግራ ደካማ ነው። በዘመነ ኦሪትም ድካመ ነፍስ የነበረበት፤ ቅዱስ ኢሳይያስ “እስመ ጽድቅነ ኮነ ከመ ጽድቀ ትክቶ - ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆነ” /ኢሳ፤ 64፣6/ እንዳለው ሰዎች በነበራቸው ጽድቅ የማይጠቀሙበት ዘመን ነበርና በግራ ተመስሏል። ቀኝ የዘመነ ሐዲስ ምሳሌ ነው። ቀኝ ኀይለኛ ነው። ቢመታ ያደቃል፣ ቢወረውር ያርቃል፣ ቢይዝ ያጠብቃል። በዘመነ ሐዲስም ኀይለ ነፍስ እንጂ ድካመ ነፍስ የለም። ድካመ ነፍስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተወግዶልን ኀይለ ነፍስ አግኝተናል።
በመጀመሪያ በግራ ማኅጸኗ ሶስት ወፍ፣ አምስት ወፍ፣ አስራ አምስት ወፍ፣ አርባ ስድስት ወፍ፣ ሰባ ሁለት ወፍ ማስገኘቷ

·         ሶስት ወፍ … የሶስቱ አርዕስተ አበው የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ ምሳሌ፤

·         አምስት ወፍ … የአምስቱ መጻሕፍተ ሙሴ፦ የኦሪት ዘፍጥረት፣ ዘጸአት፣ ዘኊልቁ፣ ዘሌዋውያንና ዘዳግም ምሳሌ፤

·         አስራ አምስት ወፍ … የአስራ አምስቱ ነቢያት ምሳሌ፤

·         አርባ ስድስቱ ወፍ … የአርባ ስድስቱ መጻሕፍተ ብሉያት ምሳሌ፤

·         ሰባ ሁለቱ ወፍ … የሰባ ሁለቱ ሊቃናት /አርባ ስድስቱን መጻሕፍተ ብሉያትን ወደ ጽርዕ /ግሪክ/ የተረጎሙ አበው ሊቃውንት ምሳሌ ነው።
እነዚህ አዕዋፍ ለአርባ ቀን በእግራቸው ተሽከርክረው ከዛም በክንፋቸው እንደበረሩት ሁሉ አርባ ስድስቱ መጻሕፍተ ብሉያት በብሉይ ኪዳን ዘመን ሥጋውያን ሁነው /በእግር መሽከርከር የሥጋውያን ምሳሌ ነው/ ሲነገሩ ኑረው በኋላ በሐዲስ ኪዳን ግን መንፈሳውያን ሁነው /በክንፍ መብረር የመንፈሳያን ምሳሌ ነው/ ከመነገር አልፈው ሲሰበኩ፣ ሲተረጎሙ የመኖራቸው ምሳሌ ነው።

በቀኝ ማኅጸኗ አስራ ሁለት፣ ሰላሳ አምስት፣ ሰባ ሁለት እንቊ ማስገኘቷ እንደዚሁ ምሳሌ ያለው ሲሆን

·         አስራ ሁለት እንቊ … የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ምሳሌ፤

·         ሰላሳ አምስት እንቊ … የሰላሳ አምስቱ መጻሕፍተ ሐዲሳት ምሳሌ፤

·         ሰባ ሁለቱ እንቊ … የሰባ ሁለቱ አርድእት ምሳሌ፤

·         በመጨራሻ የሚገኘው ክቡር እንቊ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው።

ከዖፈ ብርጋና /ከርከዴዴን/ ምን እንማራለን?
ከዚህች ዖፈ ብርጋና ወይም ከርከዴዴን /ሰደፍ/ የምንማረው በርካታ ነገር ቢሆንም በተለይም ክብረ ድንግል ማርያምን እንማርባታለን። ከርከዴዴን ንጽህት እምነ አዕዋፍ ናት፤ እግዝእትነ ማርአምም ንጸህት እምልማደ አንስት /ከሴቶች ልማድ የተለየች/ ናት። ቅዱስ ገብርኤል “ቡርክት አንቲ እምሰንስት - አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ” እንዳላት /ሉቃ፤ 1፣28/ ቅድስት ኤልሳቤጥም “ወብጽእት አንቲ እንተ ተአምኒ ከመ ይከውን ቃል ዘነገሩኪ እምኀበ እግዚአብሔር - ከሴቶች ተለይተስ አንቺ የተባረክሽ ነሽ … ከእግዚአብሄር ዘንድ የነገሩሽ ቃል እንደሚሆን የምታምኚ አንቺ ብፅእት ነሽ” ሉቃ፤ 1፣45 እንዳለቻት፤ ቅዱስ ያሬድም “ማርያምሰ ተኀቱ ውስተ ከርሱ ለኣዳም ከመ እንቆ ባሕርይ - እመቤታችን ማርአም ከአዳም ዘር የተለየች ተመረጠች ናት” /ድጓ/ እንዳለው።
ዖፈ ከርከዴዴን ያለ ወንድ ዘር በፀሐይ ጸዳል እንደጸነሰች ሁሉ እግዝእትነ ማርያምም እንበለ ዘርዓ ብእሴ - ያለ ወንድ ዘር ጸንሳለች። ልክ እንደ ጸዳለ ፀሐይ እመቤታችን በሰሚአ ቃለ መልአክ - የመልአኩን ድምጽ “መንፈስ ቅዱስ ይመጽዕ ላዕሌኪ ወኀይለ ልዑል ይጼልለኪ ዘኒ ይትወለድ እምኔኪ ቅዱስ ውእቱ - መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ የልዑል ኀይልም ይጋድርሻል ካንቺ የሚወለደው ቅዱስ ነው።” /ሉቃ፤ 1፣35/ የሚለውን ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ጸንሳ ተገኝታለች። “ወተረክበት ጽንስተ ዘእመንፈስ ቅዱስ - በመንፈስ ቅዱስ ጸንሳ ተገኘች” እንዳለ ቅዱስ ማቴዎስ /ማቴ፤ 1፣18/
ዖፈ ከርከዴዴን ሶስት ማዕረግ ከፍ ብላ በጸሀይ ጸዳል እንደተመታች፣ ከዛም ወደ ባህር ጠልቃ እንደጸነሰች ሁሉ እግዝእትነ ማርያምም ሶስተኛ ትውልድ አልቆ በአራተኛው ትውልድ ጌታን የመውለዷ ምሳሌ ነው። እነዚህ አስራ አራቱን ትውልድ አንድ፣ አንድ ተደርገው ተቆጥረው የተገኙ ናቸው።፡ከአብርሃም እስከ ዳዊት፣ ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ፣ ከባቢሎን ምርኮ እስከ ክርስቶስ ያሉት ናቸው። /ማቴ፤ 1፣17/

ዖፈ ከርከዴን ሌሎቹን እንቊ አስገኝታ በመጨረሻም የከበረ እንቊ አስገኝታለች። ይህም የከበረ እንቊ የኢሱስ ክርስቶስ ምሳሌ እንደ ሆነ ተመልክተናል።፡እንቊ የጌታ ምሳሌ ከሆነ የእንቊው መገኛ የሆነችው ዖፈ ከርከዴዴን ደግሞ የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ወልድ ይትሜሰል በእንቆ ባሕርይ - ወልደ እግዚአብሔር በእንቆ ባሕርይ ወይም በከበረ ወርቅ እየመሰለ አስተምሯል። ሰደፍ ወይም ከርከዴዴን ያለ ዘር እንቊ ባሕርይ ጸንሳ እንደተገኘች ሁሉ እንደ እንቊ ንጹሀ ባሕርይ የሆነውን ጌታን የወለች ድንግል ማርያም ያለ ዘርአ ብእሴ ጸንሳ መገኘቷንና ለዚህም እጹብ ድንቅ ለሆነው የድንግል ማርያም የጽንስ ሁኔታ ምስክርነት ትሰጥ ዘንድ ሰደፍን /ከርከዴዴንን/ ይጠራታል። “ይትናገር ሰደፍ ዘውእቱ አስከሬነ እንቊ ባሕርይ በእንተ ልደቱ ለእንቊ ባሕርይ - የእንቊ ባሕርይ መገኛ ሰደፍ የእንቊ ባሕርይን መገኘት ይናገር፤ በባሕር የሚገኘው ሰደፍ አንደምን እንደሚጸንሰው ይናገር፤ ለሰው መምህር ይሁን” /ሃይ. አበው/ በማለት የጌታን በድንግልና ተጸንሶ መወለድ፣ የድንግል ማርያምን በድንግልና ጸንሳ መውለዷን ለማያምኑ መናፍቃን ሰደፍ ወይም ከርከዴዴን ምስክርንት እንዲሰጥ ይጠይቃል።

ማስታወሻ
በዓለማችን ላይ የተለያዩ የእንቊ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቦ የምናገኛቸው የእንቁ ዓይነቶች አስራ ሁለት ናቸው። እነዚህም፦ እንቊ ኢያሰጲድ፣ እንቊ ሰንፔር፣ እንቊ ኬልቄዶን፣ እንቊ መረግድ፣ እንቊ ሰርዶንክስ፣ እንቊ በሰርድዮን፣ እንቊ ክርስቲሎቤ፣ እንቊ ቢረሌ፣ እንቊ ወራውሬ፣ እንቊ ክርስጵራስስ፣ እንቊ ያክንት፣ እንቊ አሜቴስጢኖስ ናቸው። ራዕይ፤ 21፣19   

 

----------------------------------------------------------------------------------------------------------

የዕለተ ዓርብ ሥነ ፍጥረት

ዓርብ ዐረበ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ተካተተ ማለት ነው። ስለዚህ ዓርብ ማለት መካተቻ መደምደሚያ ማለት ነው። ምዕራብ ስንል መግቢያ፣ መጥለቂያ /ለምሳሌ የፀሐይ መግቢያን ምዕራብ የምንለው ለዚህ ነው/ ማለት ሲሆን ዐረብ ሲባልም ተመሳሳይ ነው። ከኢየሩሳሌም ምዕራባዊ አቅጣጫ ያሉ ሀገራት የዐረብ ምድር ይባላሉ። ዐርብ የተባለበት ምክንያት በዕለተ እሑድ መፈጠር የጀመሩት ፍጥረታት ተፈጥረው ያበቁበት /የተካተቱበት/ ቀን ስለሆነ ዐርብ ወይም መካተቻ ተብሏል። ዕለተ ዓርብ ለሥነ ፍጥረት ስድስተኛ፣ ለጥንተ ቀመር አምስተኛ፣ ለጥንተ ዮን አራተኛ ቀን ነው።
በዚህ ቀን እግዚአብሔር “ወይቤ እግዚአብሔር ለታውፅዕ ምድር ዘመደ እንስሳ ወዘይትሐወስ ወአራዊተ ምድር በበዘመዶሙ - እግዚአብሔር አለ፦ ምድር ሕያዋን ፍጥራታትን እንደ ወገኑ እንስሳትን ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ።” ዘፍ፤ 1፣24 በዚህን ጊዜ ሶስት ፍጥረታት በየወገናቸው ተፈጥረዋል። እነዚህም ልክ እንደ ሐሙስ ፍጥረታት በእግር የሚሽከረከሩ፣ በልብ የሚሳቡ እና በክንፍ የሚበሩ ናቸው። ከዕለተ ሐሙስ ፍጥረታት የሚለዩት የሐሙስ ፍጥረታት ከባሕር የተገኙ ሲሆን የዓርብ ፍጥረታት ደግሞ ከየብስ ወይም ከመሬት የተፈጠሩ ናቸው። የሐሙስና የዓርብ መሆናቸውን የምንለየውም በአኗኗራቸው ሲሆን የሐሙስ ፍጥረታት በባሕር /aquatic animals/፤ የዓርብ ፍጥረታትም በየብስ / terrestrial animals / ይኖራሉ። ስለምን በባሕርና በየብስ አድርጎ ፈጠራቸው? ቢሉ አምላከ ባሕር ወየብስ ነኝ ሲል ነው። በዚህ ቀን በአራተኛ አዳምን ፈጥሯል። ይህንን በኋላ እንመለስበታለን።


ከዕለተ ዓርብ ፍጥረታት ምን እንማራለን?
በዕለተ ሐሙስ ምስጢረ ጥምቀትን እንደተማርን ሁሉ ከዕለተ ዓርብ ፍጥረታት ደግሞ ምስጢረ ትንሳኤ ሙታንን ተምረናል። ሰው ነፍሱ ከሥጋው ስትለይ መልካም የሰሩ በመላእክተ ብርሃናት አማካኝነት በገነት፣ ክፉ የሰሩ ደግሞ በመላእክተ ጽልመት አማካኝነት ወደ ሲዖል ተወስደው በእነዚህ ዓለማተ መሬት ይቆያሉ። በዕለተ ምጽዓት ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ሲመጣና “ንቃሕ መዋቲ ዘትነውም - ሙታን ተነሱ!” ባለ ጊዜ ፍጥረታት መነሳት ይጀምራሉ። የዕለተ ዓርብ ከየብስ በተፈጠሩት ፍጥረታት ልክ ሶስት ጊዜ ንፍሐተ ቀርን ይደረጋል።

በልብ መሳብ የመጀመሪያ ንፍሐተ ቀርን “በቀዳሚ ንፍሐተ ቀርን ይትጋባእ ጸበለ ሥጋ ዘተዘርወ ውስተ ኩሉ አጽናፈ ዓለም - በመጀመሪያ አዋጅ በዓለም ዙሪያ የተበተነ የሥጋ ዘር ይሰበሰባል።”፤ በእግር መሽከርከር የሁለተኛ ንፋተ ቀርን “ወበዳግም ንፍሐተ ቀርን ይሰፈያ አዕፅምት ምስለ ሥጋ ወይከውን በድነ ፍጹመ ዘእንበለ አንሳሕስሖ ወኢተሐውሶ እስከ ጊዜሁ - በሁለተኛ አዋጅ ሙታን ወደቀደመ መገናኛው ይመለሳል /ሥጋ ከአጥንት ጋር ይገናኛል/ ያለመንቀሳቀስ ያለመለወጥ ፍጹም በድን ይሆናል።”፣ በክንፍ መብረር የሶስተኛ ንፋተ ቀርን ምሳሌ ነው። “ወበሳልስ ንፍሐተ ቀርን ይትነስኡ ሙታን ከመ ቅጽበተ ዓይን ጻድቃን ወኃጥአን እንዘ ይጸውሩ ምግባራቲሆሙ እምዲበ ምድር ዘተለዎሙ እመሂ እኩየ ወእመሂ ሠናየ - በሶስተኛው አዋጅ ሙታን እንደ ዓይን ጥቅሻ ይነሳሉ። /ቅዳሴ ያዕቆብ ዘስሩግ/ ስለዚህ በልብ መሳብ የመሰብሰብ፣ በእግር መሽከርከር የፍጹም በድን መሆን፣ በክንፍ መብረር የትንሳኤ ምሳሌ ነው። አንድም በልብ መሳብ የፍጹም በድን የመሆን ምሳሌ፣ በእግር መሽከርከር የትንሳኤ /የመነሳት/ ምሳሌ፣ “ወበደሃሪ ንፍሐተ ቀርን ይትነስኡ ሙታን እንዘ ይትከነዩ - የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን” 1ኛ ቆሮ፤ 15፣52 በክንፍ መብረር የተመስጦ “ከዚህ በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፣ ጌታን በአየር ሆነን ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤” 1ኛ ተሰ፤ 4፣17

ንፋተ ቀርን ማለት እንደ አባቶቻችን ትርገሜ መለከት ተይዞ እንደ ጥሩንባ ይነፋል ማለት አይደለም። ይህ ማለት አንድም አዋጅ ሲታወጅ ማለትም እግዚአብሔር “ንቃህ መዋቲ ዘትነውም!” ብሎ ሲናገር ማለት ነው። አንድም እግዚአብሔር “ንቃሕ መዋቲ ዘትነውም!” ሲል መላእክት በመጀመሪያ አዋጅ “ቅዱስ እግዚአብሔር ዘያነቅሖሙ ለሙታን” ብለው በታላቅ ድምጽ ያሰማሉ፣ በሁለተኛ አዋጅ “ቅዱስ ኃያል ዘያነቅሖሙ ለሙታን” ፣ በሶስተኛው አዋጅ “ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘያነቅሖሙ ለሙታን” ብለው ስለሚያሰሙ ነው። ቅዱስ ጳውሎስም የእግዚአብሔር አዋጅ በመላእክት ቃል እንደሚታጀብ ሲናገር “እስመ ይኤዝዝ እግዚእነ ምስለ ቃለ ሊቀ መላእክት ወንፍሐተ ቀርን ዘእግዚአብሔር -ጌታ እራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምጽ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳል” ይላል። 1ኛ ተሰ፤ 4፣16  

በባሕር የተፈጠሩት ደግመው በየብስ መፈጠራቸው በጥምቀት የወለድኳቸውን በትንሳኤ እወልዳችኋለው ሲል ነው። ይህም ማለት ዳግም ሲመጣ በትንሳኤ ዘለክብር አስነሳቸዋለሁ ሲል ነው። “ወዘንተ ባሕቱ አእምሩ ኩልክሙ ከመእለ ተጠመቅነ በእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ውስተ ሞቱ ተጠመቅነ ወተቀበርነ ምስሌሁ ውስተ ጥምቀት - በሞቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከትንሳኤው ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?” ሮሜ፤ 6፤6

የሰው ልጅ ተፈጥሮ
ሥላሴ በዕለተ ዓርብ በነግህ “ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ - ሰውን በመልካችንና በምሳሌያችን እንፍጠር” በማለት አራቱን ባሕርያተ ሥጋና ሶስቱን ባሕርያተ ነፍስ አዋሕደው አዳምን በማዕከለ ምድር በቀራንዮ /ኤልዳ/ ፈጠሩት። አዳም ሲፈጠር የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ነበር። ለምን በማዕከለ ምድር በኤልዳ ፈጠሩት? ቢሉ የአዳም ባሕርይ ከሌሎች ልዩ ሲሆን ይኸውም ባሕርየ መልአክ - የመልአክ ባሕርይ እና ባሕርየ እንስሳ - የእንስሳ ባሕርይ ስላለው ማዕከላዊ ነህ ሲለው ነው። አዳም እንስሳዊ ባሕርያት አሉት ማለት መብላት፣ መጠጣት፣ መተኛት፣ መሞት … ወዘተ አሉት ማለት ሲሆን መልአካዊ ባሕርያት ደግሞ ማስተዋል፣ መናገር፣ ዘላለማዊነት /ሞቶ አለመቅረት/ ባሕርያት አሉት ማለት ነው።

በመልካችንና በአምሳላችን እንፍጠር ማለታቸው ለሥላሴ እንደ ሰው ግዙፍ የሆነ አካል ባይኖራቸውም ረቂቅ በሆነው አካላቸው ላይ በሰው ላይ ያለው መልክ አላቸውና ነው። አንድም ሥላሴ ዘላለማውያን ስለሆኑ አዳምም የማትሞት ሕያዊት የሆነች ነፍስ ስላለው ነው። አንድም በአንድነትና በሶስትነት ይመስላቸዋልና ነው። ሥላሴ ለባውያን፣ ነባብያን፣ ሕያዋን እንደሆኑ ሁሉ አዳምም ነባቢት፣ ለባዊት፣ ሕያዊት ነፍስ አለው። ሥላሴ ለባውያን፣ ነባብያን፣ ሕያዋን ቢሆኑም ሶስት አማልክት አይባሉም። እንደዚሁ ሁሉ አዳምም ለባዊ፣ ነባቢ፣ ሕያዊ ስለሆነ ሶስት ሰው አይባልም። አንድ ሰው ይባላል እንጂ።

አዳም ማለት ያማረ፣ የሰመረ፣ የተዋበ፤ እንደ ረዓይት /እጅግ በጣም ረዥም የነበሩ/ ሳይረዝም፤ እንደ ድንክ ሳያጥር የተፈጠረ፤ ይህ ቀረህ የማይባል እጅግ መልከ መልካም ማለት ነው። አንድም ዘተሰገወ እምድር - ከመሬት የተገኘ /ሰው የሆነ/ ማለት ነው። አንድም “ሰብእ - ሰው” ይባላል። ሰብእ - ሰብአ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ሰባት ማለት ነው። ከሰባት ባሕርያት የተገኘ ስለሆነ ሰብእ ወይም ሰው ተብሏል። ሰባቱ አዳም የተፈጠረባቸው ባሕርያት ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ማለትም ሌሎች ፍጥረታት የተፈጠሩባቸው እሳት፣ ውሃ፣ ነፋስና መሬት ሲሆኑ ሶስቱ ደግሞ ባሕርያተ ነፍስ /ከሌሎች ፍጥረታት በተለይም ከእንስሳት የሚለዩት/ ለባዊነት /አስተዋይነት/፣ ነባቢነት /ተናጋሪነት/ እና ሕያውነት /ዘላለማዊነት/ ናቸው።
እንዲሁም እጓለ እመሕያው ይባላል። እጓል ማለት ልጅ፣ እመ /እም/ ማለት እናት ማለት ነው። ልጅ የተባለ እራሱ አዳም፣ እናት የተባለ የአዳም አስገኚ እግዚአብሔር “አንተ አቡነ ወአንተ እምነ - አንተ አባታችን አንተ እናታችን ነህ” /እንዳለ ቅዱስ ያሬድ/ እናት ሁሉን እንደምታስገኝ ሁሉ እግዚአብሔርም የሁሉ መገኛ ነው። ስለዚህ  እጓለ እመሕያው ማለት ከእግዚአብሔር የተገኘ ልጅ ማለት ነው። አንድም ሕያው የተባለ መልአክ ነው መላእክትን ከፈጠረ ከእግዚአብሔር የተገኘ ልጅ ሲለው፤ አንድም እጓል ልጅ፣ እመ /እም/ የተባለች ምድር፤ እናት ሁሉን እንደምታስገኝ ሁሉ ምድርም ሁሉን ታስገኛለች “ምድርኒ ትሁብ ፍሬሃ - ምድር ፋሬዋን ትሰጣለች” እንዲል፤ ሕያው የተባለ እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ እጓለ እመሕያው ማለት ሕያው እግዚአብሔር ከፈጠራት ምድር የተገኘ ልጅ ማለት ነው።
እግዚአብሔር አምላክ “ንግበር ሰብአ” ባለ ጊዜ ነፍስና ሥጋው በአንድ ጊዜ ተዋሕደው ተፈጥረዋል። “ወገብሮ እግዚአብሔር ለሰብእ እመሬተ ምድር ወነፍሐ ውስተ ገጹ መንፈሰ ሕይወት ወኮነ እጓለ እመሕያው - እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፣ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት።”

ሃያ አንዱን ፍጥረታት ከፈጠረ በኋላ እርሱን ሃያ ሁለተኛ አድርጎ በመጨረሻ ለምን ፈጠረው? የሚል ጥያቄ ብንጠይቅ የዚህ ምክንያቱ አንድ ሰው እቤቱ እንግዳ ሲጋብዝ አስቀድሞ የሚበላውን፣ የሚጠጣውን አዘጋጅቶ ነው እንጂ እንግዳው ከገባ በኋላ አይደለም ማዘጋጀት የሚጀምረው። እንደዚሁ ሁሉ እግዚአብሔርም ለአዳም የሚያያስፈልገውን የሚበላውን፣ የሚጠጣውን፣ የሚገዛው፣ የሚነዳውን ሁሉ ካዘጋጀ በኋላ ፈጠረው።

ሌሎችን እንስሳት ስንመለከት ሁሉም ጎንበስ ብለው የተፈጠሩ መሆናቸውን እናስተውላለን፤ ነገር ግን አዳምን ቀና አድርጎ ከሌሎቹ ለይቶ ፈጥሮታል። ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን ለአብነት ያህል አዳምን ገዢ፣ ሌሎችን ተገዢ ናችሁ ሲላቸው፤ አንድም አዳም ሞቶ፣ ፈርሶ፣ በስብሶ አይቀርም ከሞት በኋላ ትንሳኤ አለው፤  ሌሎችን ግን ፈርሳችሁ፣ በስብሳችሁ ትቀራላችሁ ሲላቸው እርሱን ቀጥ አድርጎ፣ እንስሳትን አጎንብሰው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል። አዳም ቀና ማለት ብቻ ሳይሆን የሚቆምም የሚቀመጥም፤ የሚተኛ የሚነሳ አድርጎ ነው የፈጠረው። መቆሙ ሰማያዊ ነህ ሲለው፤ መቀመጡ ምድራዊ ነህ ሲለው ነው። በመተኛቱ በዚህ ዓለም መዋቲ መሆኑን፣ በመነሳቱ በወዲያኛው ዓለም የመነሳቱ ምልክት ነው።አዳም በተፈጠረ በስምንተኛው ቀን፣ በሶስት ሰዓት ሔዋን ተፈጠረች። “ወይቤ እግዚአብሔር ኢኮነ ሠናየ ለእጓለ እመሕያው ይንበር ባሕቲቶ አላ ንግበር ሎቱ ቢጸ ዘትረድኦ - አዳምን ብቻውን ይኖር ዘንድ አይገባውም ረዳትን እንፍጠርለት” ዘኊ፤ 2፣18 ዘይረድኦ - የሚረዳው ማለቱ ስለምን ነው? ቢሉ ልጅ በመውለድ፣ በአቅልሎ ክበደ ዋዕይ /በሀዘን ጊዜ በማጽናናት/ እንዲሁም እርሱ በሜዳ፣ እርሷ በጓዳ፤ እርሱ የአፍአውን /የውጪውን/፣ እርሷ የውስጡን በማከናወን ይረዳዳሉ። ሁለቱም ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ በምክረ ከይሲ ሕገ እግዚአብሔርን አፍርሰው ከገነት ተባረዋል። ይቆየን!

 

----------------------------------------------------------------------------------------------------------

የሐሙስ ሥነ ፍጥረት

ሐሙስ የሚለው ሐመሰ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን አምስት አደረገ ማለት ነው። ለሥነ ፍጥረት አምስተኛ ቀን ስለሆነ ሐሙስ ተብሏል። ከዚህ ቀደም እንደተመለከትነው ረቡዕ ለሥነ ፍጥረት አራተኛ፣ ለቀመር ሁለተኛ፣ ለጸሐይ /ለጥንተ ዮን/ አንደኛ ቀን ነው ብለናል። በዚሁ መሰረት ሐሙስ ለሥነ ፍጥረት /ለጥንተ ዕለት/ አምስተኛ፣ ለቀመር ሶስተኛ፣ ለፀሐይ /ለጥንተ ዮን/ ሁለተኛ ቀን ነው። በዚህ ቀን እግዚአብሔር “ለታውጽዕ ማይ ዘይተሐወስ ዘቦ መንፈሰ ሕይወት ወአዕዋፍ ዘይሰርሩ መልዕልተ ምድር ወመትሕይተ ሰማይ ወኮነ ከማሁ - እግዚአብሔር አለ፦ ውሃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾችን ታስገኝ፣ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ በታች ይብረሩ።” ዘፍ፤ 1፣20
“ወአመ አዘዛ እግዚአብሔር ለባሕር አውጽአት ኩሉ ዘመደ እንስሳ ወአራዊተ ወአዕዋፈ አበይተ ወደቃቀ ዘአልቦ ሁልቊ - እግዚአብሔርም ታላላቅ አንበሪዎችን ውሃይቱ እንደወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ እንደወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ።” ዘፍ፣ 1፣21 በዚህን ጊዜ፦

·         በእግር የሚሽከረከሩ፣

·         በልባቸው የሚሳቡ፣

·         በክንፋቸው የሚበሩ በየወገኑ በየወገኑ አድርጎ ሶስት ፍጥረታትን በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ ከባሕር ፈጠራቸው።


እነዚህ ፍጥረታት ከተፈጠሩ በኋላ ሁሉም በባሕር ውስጥ አይውሉም። በባሕር ፀንተው የሚኖሩ አሉ፤ ከባሕር ወጥተው በየብስ ውለው በባሕር ተመልሰው የሚያድሩ አሉ፤ ከተፈጠሩም በኋላ በርረው በየብስ የቀሩ አሉ። እንዲሁም በእግር የሚሽከረከሩ፣ በልብ የሚሳቡ፣ በክንፍ የሚበሩ አሉ።

እነዚህ አምሳልና መርገፍ ናቸው፤ ማለትም ምሳሌ አላቸው። ምሳሌነታቸውም፦

1ኛ. በባሕር ውስጥ ጸንተው የሚኖሩት፦

·         በእምነታቸው ጸንተው፣ በእግዚአብሔር አምነው የሚኖሩ ምሳሌ፣

·         አንድም በሕገ እግዚአብሔር ጸንተው በትዳር ተወስነው በሀብት በንብረታቸው መልካም ስራ እየሰሩ ማለትም ለቤተ እግዚአብሔር አንጽፈው፣ መስዋዕት አቅርበው፣ አስራታቸውን /ከደሞዛቸው ከአስር አንድ / በኩራታቸውን /ከሰውና ከእንስሳ በመጀመሪያ የተገነውን ለቤተ እግዚእብሔር ለግሰው/ ቀዳማያት/ከሰብላቸው፣ ከአዝርዕታቸው ቀዳሚውን ሰጥተው/ የሚኖሩ በሕግ ጋብቻ ተወስነውና ጸንተው ሚኖሩ ሰዎች ምሳሌ፣

·         አንድም ክፉ ግብራችንን አንተውም ብለው በመስረቅ፣ በመቀማት፣ ቋንጃ በመቁረጥ፣ ነፍስ በማጥፋት፣ በመዘሞት ጸንተው የሚኖሩ የኃጥአን ምሳሌ ናቸው።

2ኛ. ከባሕር ወጥተው የቀሩት ወምንት ይበቁኦ ለሰብእ ለእመ ኩሉ ዓለመ ረብኀ ወነፍሶ ሐጒለ - ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል?” በሚለው ቃል ተማርከው ይህን ዓለም በመናቅ ከዘመድ ባዳ፣ ከሀገር ምድረ በዳ ከሕገ ሰብእ ሕገ መላዕክት፤ ከተግባረ ስጋ ተግባረ ነፍስ ይሻለናል ብለው ይህን ዓለም ንቀው በገዳማት በሰድባራት ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ የሌሊት ቁሩን የቀን ሐሩር፣ ግርማ ሌሊቱን፣ ድምጸ አራዊቱን ታግሰው ዳባ ለብሰው፣ ዳዋ ጥሰው፣ ከደል ወድቀው፣ ከዛፍ ስር ተጠግተው የሚኖሩ የመናንያን መነኮሳት ምሳሌ ነው። ዕብ፤ 11፣35 

3ኛ. አንዴ በባሕር አንዴ በየብስ ወጣ ገባ እያሉ የሚኖሩት

·         አንድ ጊዜ ወደ ገዳም፣ ዕጸበ ገዳም ሲያስቸግራቸው እንድ ጊዜ ወደ ዓለም ወጣ ገባ እያሉ የሚኖሩ የመነኮሳት ምሳሌ፣

·         አንድ ጊዜ ወደ ሃይማኖት አንድ ጊዜወደ ክህደት የሚሄዱ የምዕመናን ምሳሌ፣

·         አስሩ ማዕረጋት /አስሩ ማዕረጋት የሚባሉት ጽማዌ፣ ልባዌ፣ ጣዕመ ዝማሬ፣ ሑሰት፣ ፍቅር፣ አንብዕ፣ ንጻሬ መላዕክት፣ ተሰጥሞ፣ ከዊነ እሳት፣ ነጽሮተ ስሉስ ቅዱስ/ ደርሰው ተመልሰው አቡነ ዘበሰማያት ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ - አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር … በደላችንን ይቅር በለን/ ብለው የሚለምኑ ሰዎች ምሳሌ ነው።

እንዲሁም ከእነዚህ ፍጥረታት ውስጥ በእግር የሚሽከረከሩ፣ በልብ የሚሳቡ እና በክንፍ የሚበሩ አሉ። ይኸውም፦

·         በእግር መሽከርከር የመንግስት ምሳሌ፣

·         በልብ መሳብ የክህነት ምሳሌ፣

ክህነት የዐቢ እመንግስት - ክህነት ከመስፍንነት ይበልጣል ምሳሌ፤ 26፣7

·         በክንፍ መብረር የጥምቀት ምሳሌ ነው። አንድም፡

·         በእግር የሚሽከረከሩ የመነኮሳት፣

·         በልብ የሚሳቡ የሕጋውያን /በቅዱስ ጋብቻ የሚኖሩ/ የሰብኣ ዓለም ምሳሌ፣

·         በክንፍ የሚበሩ የሰማዕታት ምሳሌ ናቸው።

ከዕለተ ሐሙስ ፍጥረታት ምን እንማራለን?

በአጠቃላይ ከእለተ እሑድ ፍጥረታት ምስጢረ ስላሴን፣ ከእለተ ሰኑይ ፍጥረታት ምስጢረ ሥጋዌን፣ ከዕለተ ሰሉስ ፍጥረታት ሃይማኖትንና ስነ ምግባርን፣ ከዕለተ ረቡዕ ፍጥረታት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደተማርን ሁል ከዕለተ ሐሙስ ፍጥረታት ምስጢረ ጥምቀትን እንማራለን።

ከላይ እንደጀመርነው የዕለተ ሐሙስ ፍጥረታት ከባሕር ቢፈጠሩም ሁሉም በባሕር ውስጥ ጸንተው አይኖሩም። የተወሰኑት በባሕር ጸንተው የሚኖሩ አሉ። ከባህር ከወጡ መኖር የማይችሉ ለምሳሌ የዓሳ ዘር በሙሉ፤ ከባሕር ወጥተው በዛው የቀሩ አሉ፤ አንድ ጊዜ ባሕር አንድ ጊዜ የብስ እያሉ የሚኖሩ አሉ።

በባሕር ጸንተው የሚኖሩ፦ በጥምቀተ ክርስትና አምነው ተጠምቀው የሚኖሩ ምሳሌ ናቸው። “ዘኢተጠምቀ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይክል ርዕዮታ ለመንግስተ እግዚአብሔር - ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያያት አይችልም።’’ ዮሐ፤ 3፣5 “ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ዘኢአምነ ወዘኢተጠምቀ ይደየን - ያመነ የተጠመቀ ይድናል፣ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል።” ማር፤ 16፣16 

ከባሕር ወጥተው የቀሩት፦ በጥምቀተ ክርስትና አምነው ተጠምቀው ሲያበቁ በተለያየ ምክንያት ማለትም በፈተና፣ በምንፍቅና፣ በክህደት፣ ለዚህ ዓለም ባለጸግነት ብለው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ያገኙትን የእግዚአብሔር ልጅነታቸውን፣ የተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን የሚያጡ ሰዎች ምሳሌ ናቸው።

አንድ ጊዜ ከባሕር አንድ ጊዜ በየብስ የሚኖሩ፦ በጥምቀት ያገኙትን የእግዚአብሔር ልጅነት በደንብ ተረድተው ያልያዙ፤ ሲላቸው በሃይማኖት ሲያሻቸው በክህደት የሚኖሩ፤ ባካና ልቡና ይዘው እንደ ሁኔታው የሚቀያየሩ፤ በደግ ጊዜ በሃይማኖት የሚኖሩ፣ ፈተና ሲመጣ ፈተናውን ለማለፍ በሚል ሰበብ የሚክዱ ሰዎች ምሳሌ ናቸው።

የዕለተ ሐሙስ ፍጥረታት ብዛታቸው ሶስት ሲሆን በሶስት ወገን ሆነው መፈጠራቸው የሶስቱ ዐበይተ ነገድ /ታላላቅ ነገዶች/ ምሳሌ ሲሆኑ እነዚህ ሶስቱ ነገድ የሚባሉት ነገደ ሴም፣ ነገደ ያፌት፣ ነገደ ካም ናቸው። ነገደ ሴም የነገስታት ወገን፣ ነገደ ያፌት የካህናት ወገን፣ ነገደ ካም የምዕመናን ወገን ናቸው። ሶስቱንም ፍጥረታት ከባሕር እንደፈጠራቸው ሁሉ ጥምቀት ለሶስቱም ነገድ በእኩል የተሰጠች የመሆኗ ምሳሌ ነው። አንድም ጥምቀተ ክርስትና በሶስቱ የስላሴ ስሞች የመፈጸሙ ምሳሌ ነው። “ወከመ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ -  በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው።” ማቴ፤ 28፣19 ይቆየን!

 

----------------------------------------------------------------------------------------------------------

የረቡዕ ሥነ ፍጥረት

ረቡዕ ረብዓ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን አራት አደረገ ማለት ነው። ሥነ ፍጥረት መፈጠር ከጀመረ አራተኛ ቀን ስለሆነ ረቡዕ ተብሏል። ይህ ቀን ለሥነ ፍጥረት አራተኛ ቀን፣ ለቀመር ደግሞ ሁለተኛ ቀን ነው። የዕለተ ሠሉስ ፍጥረት ላይ እንደተመለከትነው ሠሉስ /ማክሰኞ/ ለቀመር የመጀመሪያ ቀን ነው። ረቡዕ ደግሞ ሁለተኛ ቀን ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ቀን እግዚአብሔር ሶስት ፍጥረታትን የፈጠረ ሲሆን “ለይኩን ብርሃን ውስተ ጠፈረ ሰማይ - በጠፈር ላይ ብርሃን ይሁን” ዘፍ፤ 1፣12 ብሎ ሲያዝ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ተፈጥረዋል። በመጀመሪያ ሰዓተ ሌሊት “ወእምዝ ነሥአ እግዚአብሔር እሳተ ወነፋሰ በበንስቲት ወገብረ ሰሌዳ ፀሐይ -  እሳትን ከኮሬብ፣ ነፋስን ከአዜብ አምጥቶ የፀሐይን ሰሌዳ ፈጥሯል።” ፀሐይ ከእሳትና ከነፋስ የተፈጠረች ሲሆን ከእነዚህ ፍጥረታት መፈጠሯ በምን የታወቃል? ቢሉ ከእሳት ለመፈጠሯ ታተኩሳለች /ታቃጥላለች/ ከነፋስ ለመፈጠሯ ትሔዳለች። “ወእምዝ ነሥአ እግዚአብሔር ነፋሰ ወማየ በበንስቲት ወገብረ ሰሌዳ ወርኅ  - በመቀጠል ውሃን ከናጌብ ነፋስን ከአዜብ አምጥቶ የጨረቃንና የከዋክብትን ሰሌዳ ፈጥሯል። ሄኖ፤ 21፣4 ይህስ በምን ይታወቃል? ቢሉ በነፋስነታቸው ይሄዳሉ፣ በውሃነታቸው ይቀዘቅዛሉ።
ዕለተ እሑድ ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩበት ቀን ስለሆነ ጥንተ ዕለት፣ ዕለተ ሠሉስ በዓለም ውስት የሚኖሩ ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩበት ቀን ስለሆነ ጥንተ ቀመር እንደተባሉት ሁሉ በዕለተ ረቡዕ ብርሃናት የተፈጠሩበት ቀን ስለሆነ ጥንተ ዮን ይባላል። ዮን ማለት ብርሃን፣ ፀሐይ ማለት ነው። “ዮን ይእቲ ስማ ለፀሐይ ሀገረ ፀሐይ ዮን ይእቲ -ዮን  ማለት የፀሐይ ስም፣ የጸሐይ ሀገር ማለት ነው።” እንዲል አረጋዊ መንፈሳዊ፤ ሶስቱ ጥንታት የሚባሉት እነዚህ ናቸው።

የፀሐይ የጨረቃና የከዋክብት ብርሃንስ ከየት የተገኝ ነው? ብለን ብንጠይቅ በዕለተ እሑድ ለይኩን ብርሃን ብሎ እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ከፈጠረው ብርሃን የስንዴ ቅንጣት ታክል ወስዶ ለሰባት በመክፈል ሶስቱን እጅ ለፀሐይ፣ ሁለቱን እጅ ለጨረቃ፣ አንዱን እጅ ለከዋክብት፣ የቀረውን አንድ እጅ ደግሞ ለማያት /ለውሆች/ እና ለደመናት ቀብቷቸዋል። ከዋክብትን ሲቀባቸው ሁሉንም እኩል አድርጎ አልቀባቸውም፤ እንደ ክብራቸው አበላልጦ ቀብቷቸዋል። የአንዱ ኮከብ ብርሃን ከሌላው ይበልጣል። “አሐዱ ኮከብ እምአሐዱ ኮከብ ይሄይስ በክብር - የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይበልጣል።” እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ፤ 15፣39
“ወአመ ተፈጥሩ ከዋክብት ሰብሑኒ ኵሎሙ መላእክትየ በዐቢይ ቃል - ቅዱሳን መላእክትም የፀሐይን ሙቀት፣ የጨረቃን ድምቀት፣ የከዋክብትን መበላለጥ አይተው ይህን ላደረገ አምላክ እልል ብለው አመስግነዋል።” ኢዮ፤ 38፣7 እንኳንስ መላእክት እግዚአብሐርም በፈጠረው ፍጥረት ደስ ብሎታል። “ወርእየ እግዚአብሔር ከመ ሰናይ - እግዚአብሔርም ያም መልካም እንደሆነ አየ” እንዲል ሙሴ ዘፍ፤ 1፣12 ቅዱስ ዳዊትም “ይትፌሳሕ እግዚአብሔር በተግባሩ - እግዚአብሔር በስራው ደስ ይለዋል” ብሏል። መዝ፤ 103፣33
እነዚህ ብርሃናት የተፈጠሩበት ዋናው ዓላማ “ወሴሞሙ እግዚአብሔር ለፀሐይ ወለወርህ ወለከዋክብት ከመ ይፍልጡ ሌሊተ እማዕከለ መዓልት ወሰዓተ እማዕከለ ዕለት ወዓመተ እማዕከለ ዘመን - መዓልቱን ከሌት፣ ሰዓቱን ከዕለት፣ ዓመቱን ከዘመን ለመለየት ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሹቸዋል።” እንዲል ኩፋሌ፤ 2፣13    
በእንተ ፀሐይ
ፀሐይን ሶስት ማዕረግ ሶስት ኬክሮስ ዝቅ አድርጎ ፈጥሯታል። ይህም ማለት በምስራቅ በኩል ፀሐይ ሶስት ኬክሮስ አብርታ በምዕራብ በኩል ትጠልቃለች። “ፀሐይኒ አዕመረት ምዕራቢሁ - ፀሐይ ምዕራቧን /መግቢያዋን/ አወቀች” እንዲል ቅዱስ ዳዊት መዝ፤ 103፣19 ሄኖ፤ 27፣4 የፀሐይ ብርሃን እንደ ጨረቃ ሕፀጽ ወይም መጉደል የለባትም። ፀሐይ በቀን ብቻ ትሰለጥናለች። “ለፀሐይ ዘአኮነኖ መዓልተ - ለፀሐይ ቀንን ያስገዛ” መዝ፤ 135፣8 ምነው ፀሐይን ቀኑን ብቻ አብርታ ሌሊቱን ሳታበራ ቀረች? ቢሉ ፀሐይ ቀኑንም ሌሊቱንም ብታበራ ኖሮ ከዋዕዩ ብዛት፣ ከሐሩሩ ጽናት የተነሳ ፍጥረቱ ሁሉ ባለቀ ነበር። ፀሐይ አውደ ዐመቱን የምታሳውቀን ሲሆን አንድ አውደ ዓመት የሚባለው በፀሐይ 365 ቀን ከአስራ አምስት ኬክሮስ ወይም ከስድስት ሰዓት ነው።
በእንተ ወርኅ /ጨረቃ/
ጨረቃ እንደ ፀሐይ ሶስት ኬክሮስ አብርታ ከምስራቅ አንስታ በምዕራብ ትገባለች። ወይትናፀሩ በገሃህ - ገጽ ለገጽ ይተያያሉ። ሁለቱ በአንድ ኆኅት /መስኮት/ ቢፈጠሩም ነገር ግን ጨረቃ ስለምታፅፅ ማለትም ስለምትሞላ ስለምትጎድል ዓመታዊ ዑደታቸው /ዙረታቸው/ እኩል አይደለም። ጨረቃ ለአስራ አራት ቀን መጋቤ ብርሃን መልአክ አላት። ይህም መልአክ ብርሃን እያወጣ ይስልባታል። ከአስራ አምስተኛ ቀን ጀምሮ ብርሃን እየተከፈለ ማለትም አንድ እጅ ብርሃን እየቀነሰ በሃያ ዘጠነኛ ቀ ጨርሳ ትጠፋለች። በዚህም ዕለት ከፀሐይ ጋር ተራክቦ ታደርጋለች። በሠላሳኛው ቀን ማጭድ መስላ በስተምስራቅ ትወጣለች። ሄኖ፤ 22፣14
ጨረቃ በአንደኛው ወር ሃያ ዘጠኝ ቀን፣ በሁለተኛው ወር ሙሉ ሠላሳ ቀን ስለምትዞር ማለትም ስድስት ወር ሃያ ዘጠኝ ቀን፣ ስድቱን ወር ደግሞ ሠላሳ ቀን ስለምትዞር ይህ በዓመት ሶስት መቶ ሃምሳ አራት ቀን ይሆናል። እነዚህ የጨረቃ ዓመታዊ ዑደት እንደ ፀሐይ ሶስት መቶ ስልሳ አምስት ቀን ሳይሆን ሶስት መቶ ሃምሳ አራት ቀን ብቻ ነው።    
 በእንተ ከዋከክብት
ከዋክብት ከላይ እንደተመለከትነው እንደ ክብራቸው የብርሃናቸው መጠን ይለያያሉ። ከዋክብት ከጨረቃ ጋር አብረው በሌሊት በመሰልጠን ለሌሊቱ ድምቀትን፣ ግርማ ሞገስን ያጎናጽፋሉ። ከዋክብት ብዙ ዓይነት ስለሆኑ ከዚህ ቀጥሎ ለባሕረ ሐሳብ ትምህርታችን የሚጠቅሙንን መገብተ ከዋክብት የሚባሉትን ብቻ እንመለከታለን።
መገብተ ከዋክብት
ከከዋክብት መካከል ዕለትን፣ ወርኅን እና ወቅትን የሚመግቡ፣ የሚመሩ ከዋክብት ተሹመዋል። የእነዚህን ከዋክብት ስማቸውን ከዚህ ቀጥሎ እንመለለከታቸዋለን።
1.    መገብተ ዕለት፦ መገብተ ዕለት የሚባሉት ከዋክብት ብዛታቸው በሳምንቱ ዕለታት ልክ ሰባት ናቸው። እነዚህም ሸምሽ፣ ቀመር፣ መሪህ፣ መስተሪህ፣ ዙሀል፣ አጣርድ እና ናርድ ይባላሉ። እያንዳንዳቸው እንደቅደም ተከተላቸው ከሰኞ እስከ ዐርብ ያሉትን ቀናት ይመግባሉ። ለምሳሌ ሸምሽ ሰኞን፣ ቀመር ማክሰኞን … ናርድ አርብን ይመግባሉ።
2.   መገብተ አውራኅ፦ እነዚህም በአስራ ሁለቱ ወራት ልክ አስራ ሁለት ናቸው። እነርሱም አልሐመል፣ አልሰውር፣ አልጃሙዛ፣ አልሸርጣን፣ አልሰአድ፣ አልሰንቡላህ፣ አልሚዛን፣ አልአቅረብ፣ አልቀውስ፣ አልዛዲፍ፣ አልደለው፣ አልሃት ይባላሉ። እነዚህም እያንዳንዳቸው በዓመት ውስጥ ያሉትን ወራትን ይመግባሉ። ለምሳሌ አልሐመል መስከረምን፣ አልሰውር ጥቅምትን፣ … አልሃት ነሐሴን ይመግባሉ ማለት ነው።
3.   መገብተ ወቅት፦ እነዚህም ታላላቅ ከዋክብት ሲሆኑ በዚህም የተነሳ ሊቃነ ከዋክብት /የከዋክብት አለቆች/ ይባላሉ። የእነዚህ ቁጥርም በዓመቱ ውስጥ ባሉ ወቅቶች ልክ አራት ናቸው። በዓመት ውስጥ ያሉት አራቱ ወቅቶች የሚባሉት ክረምት፣ መፀው /መኸር ወይም መከር/፣ ሐጋይ /በጋ/ እና ፀደይ /በልግ/ ናቸው። አራቱ ሊቃነ ከዋክብት የሚባሉት ናርኤል፣ ብርክኤል፣ ምልኤል እና ኅልመልሜሌክ ናቸው።፡እነዚህም እያንዳንዳቸው አራቱን ወቅቶች በየተራ ይመግባሉ።
እነዚህ ከዋክብት ማለትም መገብተ ዕለት ከዋክብት በየሳምንቱ፣ በገብተ ወርኅ ከዋክብት በየዓመቱ፣ መገብተ ወቅት ከዋክብት በየሶስት ወራቱ የሚመላለሱበትን ኆኅት /መስኮት/ አላቸው። እነዚህም መስኮቶች በምስራቅ በኩል ስድስት፣ በምዕራብ በኩል ስድስት ናቸው። ሄኖክ፤ 24፣8
ከዕለተ ረቡዕ ፍትረታት ምን እንማራለን?
በዕለተ ረቡዕ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንማራለን። ቤተርርስቲያን ስንል ሶስት ዓይነት ትርጉም ያለው ሲሆን እነዚህም የክርስቲያኖች መሰብሰቢያ የሆነው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ፣ የምእመናን አንድነቱ ወይም ስብስቡ /ማኅበረ ምዕመናኑ/ እና የእያንዳንዱ ምእመን ልቡና ቤተ ክርስቲያን ይባላል። “ወተሰምዩ አርድዕት ክርስቲያነ በአንጾኪያ ቀዲሙ - አርድት በመጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ” የሐዋ ስራ፤ 11፣27 ከሚለው ቃል የምዕመናን ስብስብ /ማኅበረ ምዕመናን/ ቤተ ክርስቲያን እንደሚባሉ ያሳየናል። “አንትሙሰ ኢታይምሩኑ ከመ ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር - እናንተ የእግዚአብሔር ቤተ መቅድስ እንደሁናችሁ አታውቁምን?” 1ኛ ቆሮ፤ 3፣10 ከሚለው የእያንዳንዱ ምዕመን ልቡና ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ክርስቲያን እንደሚባል እንመለከታለን።
ስለዚህ በዚህ ቀን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንማራለን ስንል በምእመናኑም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ሥርዓት እንማራለን ማለታችን ነው።
ፀሐይ ሁልጊዜ ሙሉ ስለሆነች የጻድቃን ምሳሌ ናት። ጻድቃን በምግባር በሃይማኖት ዘወትር ምሉዕ /ሙሉ/ ናቸው። ጨረቃ አንድ ጊዜ ስለምትሞላ አንድ ጊዜ ስለምትጎድል የኃጥአን ምሳሌ ናት። ኃጥአን በምግባርና በሃይማኖት እንድ ጊዜ ሲሞሉ አንድ ጊዜ ሲጎድሉ ይኖራሉ። “ልቡ ለአብድ የሐፅፅ ከመ እንተ ወርኅ - የሃጢአተኛ ልብ እንደ ጨረቃ ሲጎድል ያድራል” እንዲል ሲራክ፤ 43፤7 አንድም ፀሐይ የኃጥአን ምሳሌ፣ ጨረቃ የጻድቃን ምሳሌ፤ ጸሐይ ሁልጊዜ ምሉዕ እንደ ሆነች ሁሉ ኃጥአንም በክፉ ስራቸው፣ በክፉ ምግባራቸው፣ በክህደታቸው ምሉዓን ናቸው። ጨረቃ አንድ ጊዜ ስትሞላ አንድ ጊዜ እንደምትጎድለው ሁሉ ጻድቃንም በኃጢአት አንድ ጊዜ ሲወድቁ ሌላ ጊዜ በንስሐ ሲነሱ ይኖራሉ። “ጻድቅሰ ስብዐ ይወድቅ ስብዐ ይትነሳእ - ጻድቅ ሰው ሰባት ጊዜ ይወድቃል ሰባት ጊዜ ይነሳል:፡” ምሳሌ፤ 24፣16
በዕለተ እሑድ ከፈጠረው ብርሃን ወስዶ ለሰባት ከፍሎ የቀባቸው የሰባቱ ማዕርጋተ ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው። እነዚህም ማዕርጋተ ቤተ ክርስቲያን የሚባሉት፦ አናጉንስጢስ /አንባቢ/፣ ዲያቆን፣ ቄስ፣ ቆሞስ፣ ኤጲስ ቆጶስ፣ ሊቀ ጳጳስ እና ፓትርያርክ ናቸው።
ሶስቱም ብርሃናት ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ሲወጡ ሲገቡ ፊታቸውን ወደ ምስራቅ አድርጎ ፈጥሯቸዋል። እንደዚሁም ሁሉ ምዕመናን ፊታቸውን ወደ ምስራቅ አዙረው ለመጸለያቸው ምሳሌ ነው።
ጨረቃ ሰርቅ ካደረገች በኋላ ለአስራ አራት ቀናት መጋቤ ወርኅ መልአክ ብርሃን እያወጣ እንደሚስልባት ሁሉ ምዕመናን ከመምህራን አስሩ ቃላተ ኦሪትን፣ ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን፣ ዶግማ /ትምህርተ ሃይማኖትን … ወዘተ ሲማሩ ለመኖራቸው ምሳሌ ነው። በመጨረሻም በሃያ ዘጠነኛ ቀን መጥፋቷ መምህራን ከሞቱ በኋላ ሥልጣናቸው በእግዚአብሔር እጅ የመያዙ ምሳሌ ነው።
ለከዋክብት መመላለሻ በምስራቅ ስድስት፣ በምዕራብ ስድስት መስኮት እንዳላቸው ሁሉ ምዕመናን በስድስቱ ቃላተ ወንጌል /የሐዲስ ኪዳን/ ሕግ ፀንተው ለመመላላሳቸው፣ ለሞታቸው እና ለመነሳታቸው ምሳሌ ነው። ይቆየን

 

----------------------------------------------------------------------------------------------------------

የዕለተ ሰሉስ /ማክሰኞ/ ሥነ ፍጥረት

ሠሉስ ማለት ሶስት ማለት ነው ይህ ቀን ፍጥረታት መፈጠር ከተጀመሩ ሶስተኛ ቀን ሆኗልና ሰሉስ /ሶስተኛ/ ተብሏል።፡ ይህ ቀን ጥንተ ቀመር ይባላል። ቀመር - ቀመረ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ቆጠረ ማለት ነው። ቁጥር መቁጠር የተጀመረው በዚህ ቀን ነው። ጠቢባን ስላሴ ከዕለታት መርጠው ዓለምን የፈጠሩት በዕለተ እሑድ እና ሰኞ ሲሆን ‘ዕለተ ጠቢባን’ ይባላሉ። ዓለማት ተፈጥረው ያለቁት በእነዚህ ሁለት ቀናት ነው። ዓለማት በቁጥር ሃያ ሲሆኑ ሃያውም ዓለማት የተፈጠሩት በእነዚህ ቀናት ናቸው። በዕለተ ሠሉስ ደግሞ በሃያው ዓለማት ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩበት ዕለት ስለሆነ ጥንተ ቀመር ተብሏል።

ሃያው ዓለማት እነማን ናቸው?

ሃያው ዓለማት የሚባሉት ፦  ዘጠኙ ዓለማተ እሳት፣

                                አምስቱ ዓለማተ መሬት፣

                                 ሁለቱ ዓለማተ ነፋስ፣

                                 አራቱ ዓለማተ ማይ /ውሃ/ ናቸው።

ዘጠኙ ዓለማተ እሳት የሚባሉት፦
·         ሰባቱ ሰማያት

·         ምጽንዓተ ምድር /ከምድር በታች ያለውና መሬት የጸናችበት እሳት/

·         ገሃነመ እሳት ናቸው።

አምስቱ ዓለማተ መሬት፦
·         እኛ የምንኖርበት ምድር፦ ሶስት ስሞች ያላት ሲሆን ከውሃ ሳትለይ ፀብር /ጭቃ/፣ ከውሃ ከተለየች በኋላ ምድር /ማኅደር ወይም መኖሪያ/ ከደረቀች በኋላ መሬት ትባላለች።

·         ብሔረ ሕያዋን፣

·         ብሔረ ብጹዓን፣

·         ገነት፣

·         ሲዖል ናቸው

ሁለቱ ዓለማተ ነፋስ የሚባሉት፦
·         ባቢል፦ ከጠፈር በላይ ያለው ሐኖስን የተሸከመው ጠንካራ ነፋስ ነው።

·         በርባሮስ፦ በርባሮስ ድቅድቅ ጨለማ ሲሆን ከምድር በታች የሚገኝ እና ምድርን የተሸከመው ነፋስ የሚገኘው እዚህ ነው።
አራቱ ዓለማተ ማይ የሚባሉት፦
·         ሐኖስ፣

·         ጠፈር፣

·         ዕውቂያኖስ፣

·         ባሕር /የምድር ንጣፍ የሆነው ውሃ/ ናቸው።

እነዚህ ሃየው ዓለማት ሲሆኑ ከመላዕክት በስተቀር ሌሎች በእነዚህ ዓለማት ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት መፈጠር የጀመሩት ከዕለተ ሠሉስ ጀምሮ ነው። በዚህ ምክንያት ዕለተ ቀመር ወይም ጥንተ ቀመር እንለዋለን። በአማርኛም በተለምዶ ማክሰኞ እንለዋለን።፡በተለምዶ ማክሰኞ ብንልም ትክክለኛው ግን ማግሰኞ ሲሆን የሰኞ ማግስት ማለት ነው።

በዚህ ቀን እግዚአብሔር አምላክ ሶስት ፍጥረታትን ፈጥረል። “ወይቤ እግዚአብሔር ለታብቁል ምድር ሐመልማለ ዘርዕ ዘይዘራዕ በበዘርዑ ወበበዘመዱ - ምድር ዘርን የሚሰጥ ሳርን ቡቃያን በምድር ላይ እንደወገኑ እንደወገኑ ዘር ያለበትን፣ ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል ብሎ እግዚአብሔር አዘዘ እንዲህም ሆነ” ዘፍ፤ 1፣12 በዚህ ትዕዛዝ ሶስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል። እነሱም፦

·         በምሳር /በመጥረቢያ/ የሚቆረጡ ዕጽዋትን፣

·         በማጭድ የሚታጨዱ አዝርዕትን፣

·         በእጅ /በጣት/ የሚለቀሙ አታክልትን ከአራቱ ባሕርያት ፈጥሯል። ከአራቱ ባሕርያት መፈጠራቸው በምን

ይታወቃል ቢሉ?

      ከእሳት ለመፈጠራቸው እርስ በራሳቸው ቢያጋጯቸው እሳት ይፈጠራል፣

      ከውሃ መሆኑን ሲቆርጧቸው ውሃ ይወጣቸዋል፣

      ከነፋስ ለመፈጠራቸው በነፋስ ያድጋሉ፣

      ከአፈር ለመሆኑ ቆርጠው ቢጥለቸው ፈርሰው በስብሰው አፈር ይሆናሉ።

ሳይንሱም ቢሆን የሚስማማበት በዝናብ /በውሃ/ ይበቅላሉ፣ በነፋስ ያድጋሉ፣ በፀሐይ /እሳታዊ ናት/ ይበቅላሉ፣ ከመሬት ምግባቸውን ይወስዳሉ ይላል። ይህም አባባል እነዚህ ፍጥረታት ከአራቱ ባሕርያት መፈጠራቸውን ያረጋግጣል።

“ወተከለ እግዚአብሔር ገነተ መንገለ ምስራቅ እመልዕልተ ምድር ወታህተ ሰማይ - እግዚአብሔር አምላክ በምስራቅ በኤደን ገነትን ተከለ፤ ከምድር ከፍ ብላ ከሰማይ ዝቅ ብላ በመካከል ገነት ተተከለች።” ዘፍ፤ 2፣8-9 ከዕለተ ሠሉስ ፍጥረታት መካከል የሆኑትን ዕፀ ሕይወትን፣ ዕፀ በለስን፣ ሌሎች መልካም የሆኑ ዕጽዋት ተፈጥረዋል። ዘፍ፤ 2፣9 ሕዝ፤ 46፣13 ራዕ፤ 22፣2 በተጨማሪም “ወተከለ እግዚአብሔር አርባዕተ ዐበይተ ዕጽዋተ በዐርባዕቱ ማዕዘኒሃ ለዕፀ ሕይወት - ከዕፀ ሕይወት በአራቱ  ማዕዘንዋ አራት ታላላቅ ዕጽዋትን ተከለ” ከእነዚህም ታላላቅ ዛፎች ስር አራቱ ታላላቅ ወንዞችን አወጣ። ዘፍ፤ 2፣10 የእነዚህ አራቱ ወንዞች ስማቸው ግዮን፣ ኤፍራጥስ፣ ኤፌሶን /ፊሶን/ እና ጤግሮስ ይባላሉ። እነዚህ አፍላጋት በገነት እያሉ ወተት፣ ዘይት፣ ወይን እና ማር ሆነው ይወጣሉ። ወደዚህ ዓለም ሲመጡ ግን ንጹሕ ውሃ ሆነው ይወርዳሉ። “ሰው መልካም ምግብ በልቶ፣ ጥሩ ውሃ ጠጥቶ፣ ወደ እዳሪ ሲወጣ ተለውጦ እንዲወጣ ሁሉ እነዚህም ተለውጠው ይወጣሉ” እንዲል አክሲማሮስ /አክሲማሮስ ማለት ሥነ ፍጥረት ማለት ሲሆን ስለሥነ ፍጥረት የሚያስተምረው መጽሐፍ በስሙ ተሰይሟል/

ግዮን ፈለገ ሀሊብ /ወተት/ ነው፤ በኢትዮጵያ ይዞራል። ኤፍራጥስ ፈለገ ዘይት ነው፤ በሮምያ ይዞራል። አፌሶን ፈለገ ወይን ነው፤ በአንጾኪያ ይዞራል። ጤግሮስ ፈለገ መዓር /ማር/ ነው፤ በቁስጥንጥንያ ይዞራል። ዘፍ፤ 2፣11 በገነት ሌሎች ታላላቅና ታናናሽ ዕጽዋት ተፈጥረዋል። ፍሬያቸውም የሚምር ጣዕማቸውም ልዩ የሆኑ ናቸው። እነዚህን ዕጽዋት፤ አታክልትን ማን ይመገባቸዋል? ቢሉ በብሄረ ብጹዓን ያሉ ቅዱሳን፣ በገነት ያሉ አዕዋፍ ይመገቡታል።

ከዕለተ ሠሉስ ፍጥረታት ምን እንማራለን?

ከዕለተ ሰሉስ ፍጥረታት በርካታ ነገሮችን የምንማር ሲሆን በምሳሌ እንመለከተዋለን፦

እነዚህ ፍጥረታት በስራቸው የሚያፈሩ፣ በጎናቸው የሚያፈሩ፣ በስራቸው የሚያፈሩ አሉ። በሚስቶቻቸው /በባሎች/ በልጆቻቸው የሚጠቀሙ፤ በጌታ ትምህርት አምነው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖሩ ሰዎች ምሳሌ ነው። በጎናቸው የሚያፈሩ፦ በሰራተኞቻቸው፣ በጎረቤቶቻቸው የሚያምኑ፣ በሐዋርያት ስብከት ያመኑ፣ በጥምቀት የዳኑ ሰዎች ናቸው። በጫፋቸው የሚያፈሩት ደግሞ በራሳቸው ጥረው ግረው ራሳቸውን የሚረዱ፣ የሚያድኑ፣ እንዲሁም በሌሎች መምህራን ትምህርት ያመኑ የክርስቶስን ሞቱን፣ ትንሳኤውን አምነው በመስቀሉ የዳኑ ሰዎች ምሳሌ ነው። ሚስጥሩ ደግሞ በስራቸው የሚያፈሩ ባለ ሰላሳ፣ በጎናቸው የሚያፈሩ ባለስልሳ፣ በጫፋቸው የሚያፈሩት ባለመቶ ፍሬ የሚያፈሩ ሰዎች ምሳሌ ናቸው። ማቴ፤ 13፣1

ፍሬያቸውን በስራቸው፣ በጎናቸው በጫፋቸው የሚይዙ /የሚያፍኑ/ አሉ። በስራቸውና በጎናቸው በመሸፈን ከወፍ ከጠላት የሚከላከሉ፤ መልካም ትሩፋትን ሰርተው ነገር ግን እኛ አላደረግንም የሚሉ ቅዱሳን ምሳሌ ናቸው። ፍሬያቸውን በጫፋቸው በመያዝ ወፍ የሚበላባቸው፣ ጠላት የሚያጠፋባቸው ደግሞ የሰሩትን በጎ ስራና ትሩፋት እንዲያዩላቸው በመፈለግ፤ ይወቁልን፣ ይስሙልን የሚሉ ሰዎች ምሳሌ ናቸው። ማቴ፤ 6፣1

ከእነዚህ ፍጥረታት መካከል በአንድ መሬት ላይ በቅለው ግማሹ ጣፋጭ ፍሬ ያላቸው፣ ግማሹ መራራ ፍሬ ያላቸው አሉ። ይኸውም በአንዲት ምድር ላይ የተፈጠሩ የሰው ልጆች ግማሹ መልካም ስራ በመስራት ፈጣሪያቸውን የሚያስደስቱ ፣ ሌላው ደግሞ በመጥፎ ስራቸው በመኖር እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑ ሰዎች ምሳሌ ነው።

ዕጽዋት፣ አዝርዕት፣ አታክልት፦ አበባ የሌላቸው ፍሬ ያላቸው አሉ፣ አበባ ያላቸው ፍሬ የሌላቸው አሉ፣ አበባም ፍሬ የሌላቸው፣ አበባና ፍሬ ያላቸው አሉ።

አበባ የሌላቸው ፍሬ ያላቸው፦ ሃይማኖት ሳይኖራቸው ምግባር ያላቸው ምሳሌ ናቸው። አበባ ያላቸው ፍሬ የሌላቸው፦ ሃይማኖት ያላቸው ምግባር የሌላቸው ምሳሌ፤ አበባም ፍሬ የሌላቸው፦ ምግባርም ሃይማኖትም የሌላቸው ምሳሌ፤ አበባና ፍሬ ያላቸው ደግሞ ምግባርም ሃይማኖትም አስተባብረው የያዙ ሰዎች ምሳሌ ናቸው።

ከማክሰኞ ፍጥረታት መካከል በሰኔ ተዘርተው የክረምቱን ዝናብ ተቋቁመው ለፍሬ የሚደርሱ አሉ፤ ይኸውም ብዙ መከራና ስቃይ ተቋቁመው ለክብር የሚበቁ ቅዱሳን ምሳሌ ናቸው። እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሉ። “ንሕነሰ በብዙህ መከራ ከለወነ ከመ ንባዕ ውስተ መንግስተ እግዚአብሔር - እኛስ በብዙ መከራ የእግዚአብሐርን መንግስት እንወርሳለን” ሐዋ፤ 14፣21 በሌላ በኩል በክረምት መውጫ ተዘርተው በጥቂት ዝናብ በቅለው ለፍሬ የሚበቁ አሉ። ይኸውም በጥቂት ምግባርና ትሩፋት የሚጠቀሙ፣ እንዲሁም አንድ ቀን መከራን በመቀበል የእግዚአብሔርን መንግስት የሚወርሱ ሰዎች ምሳሌ ናቸው።

በተጨማሪም ክረምት ለምልመው በጋ የሚደርቁ፣ ክረምት ደርቀው በበጋ የሚለመልሙ ዕጽዋት፣ አታክልት፣ አዝርዕት አሉ። በክረምት ለምልመው በበጋ የሚደርቁ፤ በዚህ ዓለም ሳሉ በልተው፣ ጠጥተው፣ ለብሰው፣ ደምቀው አምሮባቸው የሚኖሩ ነገር በሚመጣው ዓለም ተስፋ ነፍስ የሌላቸው ምሳሌ ናቸው። እንደነማን? ያሉ ቢሉ እንደ ነዌ፣ እንደ ኪራ ያሉ። “ይበቁዓከ ዘከመ ፈጋዕከ በሕይወትከ - በሕይወት ሳለህ በተድላ በደስታ መኖርህን አስብ” ሉቃ፤ 16፣20 በክረምት ደርቀው በበጋ የሚለመልሙት፤ በዚህ ዓለም ተርበው፣ ተጠምተው፣ ታርዘው፣ አከው የሚኖሩ በወዲያኛው ዓለም ግን ተስፋ ነፍስ ያላቸው ናቸው። እንደነማን ? ቢሉ እንደ አልዓዛር ያሉ ናቸው። ደግሞም ክረምትም በጋም የማያፈሩ፣ የማይለመልሙ አሉ፤ እነዚህ በዚህ ዓለም ሳሉ ተቸግረው፣ አዝነው፣ ተክዘው፣ ጎስቁለው አከው የሚኖሩ ነገር ግን የደረሰባቸውን በአኮቴት የማይቀበሉ ነገር ሀጢአት በመስራት በመስረቅ፣ በመቀማት ኖረው በወዲያኛውም ዓለም ሳይጠቀሙ የዲያብሎስ ባሪያ ሆነው የሚቀሩ ሰዎች ምሳሌ ናቸው። “ድሃውን ስለድህነቱ አይምረውም እርሱን ደስ ካላሰኘው” እንዳለ ቅዳሴ አትናቴዎስ፤ ሮሜ፤ 9፣13 በሌላ በኩል በክረምትም በበጋም አፍርተው፣ ለምልመው የሚኖሩ አሉ። እነዚህም በዚህ ዓለም በተድላ በደስታ ኑረው በሃብታቸው ተግባረ ጽድቅ ሰርተውበት በወዲያኛው ዓለም የሚጠቀሙ ሰዎች ምሳሌ ነው። እነዚህ እንደ አብርሃም፣ እንደ ይስሐቅ፣ እንደ ያዕቆብ ያሉ ናቸው። ይቆየን! 

 

----------------------------------------------------------------------------------------------------------

የሰኑይ /ሰኞ/ ሥነ ፍጥረት

ሰኑይ ማለት ሁለተኛ ወይም ሁለት አደረገ ማለት ነው። ይህ ቀን ለሥነ ፍጥረት ሁለተኛ ቀን ስለሆነ  ሁለተኛ ተብሏል። አንድም ሰኑይ የሚለው ቃል ‘ሠነየ’ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወሰደ ሲሆን ይኸውም መልካም ሆነ ማለት ነው። “ወርዕየ እግዚአብሔር ኩሎ ዘገብረ ከመ ሠናይ ጥቀ - እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት መልካም እንደሆነ አየ” ዘፍ፤ 1፣12 በዚህ ቀን የተፈጠረው አንድ ፍጥረት ሲሆን ይኸውም ጠፈር ነው። በዕለተ እሑድ የተፈጠረው ውሃ ከእሑድ እስከ ሰኞ ድረስ ከምድር እስከ ብሩህ ሰማይ ኤረር ድረስ ሞልቶ ነበርና “ለይትጋባዕ ማይ ውስተ ምዕላዲሁ - ውሃ ወደ መከማቻው ይሰብሰብ” ዘፍ፤ 1፣6 በማለት እግዚአብሔር አምላክ ሲያዘው ለሶስት ተከፍሏል። አንዱን እጅ “ለይኩን ጠፈር በማዕከለ ማያት - በውሆች መካከል ጠፈር ይሁን” ዘፍ፤ 1፣9 ብሎ ውሃን እንደ ብረት አጠንክሮና አጽንቶ ጠፈርን ፈጥሮታል። አንዱን እጅ የውሃው ባሕርይ ሳይለወጥ ከጠፈር በላይ ሰቅሎ አስፍሮታል። ይኽም ሐኖስ ሲለው፤ አንዱን እጅ ደግሞ በምድር አስቀርቶታል።


በምድር የቀረውን ውሃ እንዲሁ ለሶስት የተከፈለ ሲሆን አንዱ እጅ ከምድር በታች የሰፈረው ባሕር ነው። ምድር የጸናቸው በዚህ ውሃ ነው። ቅዱስ ዳዊት “ዘአጽንአ ለምድር ዲበ ማይ - ምድርን በውሃ ላይ ያጸናህ” መዝ፤ 135፣6 እንዳለው። ሁለተኛው ምድርን እንደመቀነት የከበባት እውቅያኖስ ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ የሰው ልጅና እንስሳት የሚጠቀሙበት በየተራራው፣ በየሸንተረሩ የሚገኘው ውሃ ነው። ይህም ቀላያት፣ አፍላጋት የሚባሉት ናቸው። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የውሃ መከማቻውን ባሕር፣ የብሱን ምድር ብሎ ጠራው። ኢዮ፤ 38፣8 መዝ፤ 11፣35

የዕለተ ሰኑይን ፍጥረት ስንመለከት ሶስት ስሞችን በዋናነት አይተናል። እነዚህም ጠፈር፣ ሐኖስ እና እውቂያኖስን ተመልክተናል። ነገር ግን የዚህ ቀን ፍጥረት አንድ ብቻ ነው እንላለን። ለምን ሶስት ፍጥረት አንልም የሚል ጥያቄ በሕሊናችን ልናነሳ እንችላለን።  አዲስ ፍጥረት ተፈጠረ የሚባለው አንድ ነገር ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ ነገር ሲቀየር ወይም ሲለወጥ /Changed/ ነው። ይህም ለውጥ አካላዊና መሰረታዊ የባሕርይ ለውጥ /physical and chemical change/ መሆን አለበት። አሁን ከሶእቱ እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ የምንመለከተው በጠፈር ላይ ብቻ ነው። ምክንያቱም ጠፈር ሙሉ በሙሉ ውሃዊ ባሕርይውን ትቶ በቅርጽም፣ በመልክም ተቀይሮ፤ ፈሳሽ/liquid/ የነበረው የረጋ /solid/ ፣ እርጥብ የነበረው ይቡስ ወይም ደረቅ ፤ መልክ አልባ የነበረው መልክ ያለው ሆኗል:፡ ሌሎቹን ስንመለከት ግን እንዲህ ዓይነት ለውጥ ሳይሆን የተደረገላቸው የቦታና የአቀማመጥ ብቻ ነው። ውሃዊ ባሕርያቸው አልተለወጠም። ውሃ ደግሞ የእሑድ ፍጥረት ሆኖ ስለተቆጠረ እዚህ ጋር እንደአዲስ አንቆጥረውም። ሐኖስ ማለት ብጽብጽ ወይም ያልረጋ ውሃ ማለት ነው። ውሃው እራሱ ባህርይውን ሳይለቅ ከጠፈር በላይ አስፍሮታለ። ዕውቂያኖስም ሆነ ባህር በተመሳሳይ ሁኔታ የቦታ ለውጥ እንጂ የባሕርይ ለውጥ ስላልተደረገላቸው እንደ አዲስ ፍጥረታት አይቆጠሩም።   

ጠፈርን ከላይ እንዳየነው መልክ ያለው ሲሆን መልኩ ሰማያዊ ነው። የዚህ ምክንያቱ በርካታ ሲሆን ለአብንት ለመጥቀስ ያህል፦

1ኛ. የሰውልጅ ሰማይ ሰማዩን እያየ ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌምን እንዲያስታውስና በሰማይ ሰማያዊ ርስት እንዳለው ተስፋ እንዲያደርግ፤

2ኛ. የጠፈር መልኩ ነጭ ቢሆን ኑሮ የፀሐይ ብርሃን እያንጸባረቀ የሰዎች አይን ይጎዳ ነበር፤ መልኩ ደግሞ ጥቁር ቢሆን ዓይናችንን ይከብደንና ድንግዝዝ ይልብን ነበር ነገር ግን መልኩን ሰማያዊ አድርጎ ከነዚህ ችግሮች አድኖናል።

በተጨማሪም ጠፈር ሌሎች ጥቅምች አሉት። ጠፈርን ስንመለከተው ቅርጹ ልክ እንደ በሬ ሻኛ ጎበብ ያለ ነው።፡እንደዚህ አድርጎ የፈጠረው የፀሐይን ብርሃን ሳይነዛ ሰብስቦ እንዲይዝ ለማድረግ ነው። ነገር ግን ጠፈር ዝርግ ሆኖ ቢፈጠር ኖሮ ብርሃኑ ተነዝቶ ወደ ምድር ሳይመጣ በዛው ይቀር ነበር።

ሌላው ጠፈር ባይኖር ኖሮ የፀሐይ ብርሃን በቀጥታ በመምጣት በሰው አናት ላይ ሙሉ በሙሉ ይወድቅ ነበር። በዚህም የሰው ናላ ይዞራል፣ ሀሞት ይበተናል፣ የሰው ልጅም ሆነ ሌሎች ፍጥረታት ይጎዱ ነበር። ነገር ግን ጠፈር ቀዝቃዛ በመሆኑ የፀሐዩን ሐይል በማቀዝቀዝ ለሰው ልጅ እንዲስማማ ያደርገዋል። እንዲሁም በዕለተ ረቡዕ ብርሃናት ማለትም ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ይፈጠራሉና ለእነርሱ ማኅደር /ማደሪያ/ ፣መመላለሻ ይሆን ዘንድ ጠፈር ተፈጥሯል።

በዚህ ቀን በመጀመሪያ ሰዓተ ሌሊት ጠፈር የተፈጠረ ሲሆን ጠፈር ከተፈጠረ በኋላ የቀረውን ሃያ ሶስቱን ሰዓት ምን ሰርቶበታል ቢሉ መላእክትን ቦታ ቦታ ሰጥቶ ለአገልግሎት አሰማርቷቸዋል። ሁሉን መዘርዘር ባይቻልም የተወሰነውን ለመግለጽ ያህል፦

1ኛ. በሰማየ ኢዮር ካሉት መላእክት ከነገደ ኪሩቤል ገጸ - ሰብዕና ገጸ - አንበሳን፣ ከነገደ ሱራፌል ገጸ-ላሕምና ገጸ-ንስር መርጦ በሰማየ ውዱድ አኖራቸው። እነዚህም ፊት ለፊት አይተያዩም “አይትናጸሩ ገጽ በገጽ - ፊት ለፊት አይተያዩም” እንዲል። ራዕ፤ 4፣7

·         ገጸ - ሰብእ አቋቋሙ በምስራቅ ሆኖ ወደ ምዕራብ ያያል፤

·         ገጸ - አንበሳ አቋቋሙ በምዕራብ ሆኖ ወደ ምስራቅ ያያል፤

·         ገጸ - ላሕም አቋቋሙ በሰሜን ሆኖ ወደ ደቡብ ያያል፤

·         ገጸ - ንስር አቋቋሙ በደቡብ ሆኖ ወደ ሰሜን ያያል   ሕዝ፤ 1፣10

ነገደ ሱራፌል ባለስድስት ክንፍ ሲሆኑ ነገደ ኪሩቤል ባለ ብዙ ዓይኖች ናቸው። “ወኪሩቤል እለ ብዙኀት አዕይንቲሆሙ ወሱራፌል  እለ ስድስቱ ክነፊሆሙ” እንዲል ራዕ፤ 4፣6-8 ኢሳ፤ 6፣3 አንቀጸ ብርሃን ዘያሬድ። ሁለቱን ክንፋቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ፊታቸውን ይሸፍናሉ፣ ሁለቱን ወደታች ዘርግተው እግራቸውን ይሸፍናሉ፣ ሁለቱን ደግሞ ግራና ቀኝ በትዕምርተ መስቀል ይዘረጉታል። ወደላይ መዘርጋታቸው ቢወጡ፣ ቢወጡ አትገኝም ሲሉ፤ አንድም የተመስጦ ምልክት ነው። ወደታች መዘርጋታቸው ቢወርዱ፣ ቢወርዱ አትገኝም ሲሉ፤ አንድም የትህትና ምልክት ነው። ግራና ቀኝ መዘርጋታቸው ጽንፍ እስከ ጽንፍ ቢሄዱ ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ፤ አንድም የተልዕኮ ምሳሌ ነው። አንድም የጌታ ስቅለቱ ምሳሌ ነው። ሕዝ፤ 1፣50 ፤ ራዕ፤ 4፣6

2ኛ. በሰማየ ራማ ካሉት መላዕክት ሃያ አራት ሊቃናትን  መርጦ በመንበረ መንግስት ዙሪያ ክንፍ ለክንፍ አያይዞ አቆማቸው። የብርሃን ዘውድ ደፍተው፣ የብርሃን መስቀል ይዘው፣ የብርሃን ማዕጠንተ ወርቅ ጨብጠው የሚያመሰግኑ እና መንበሩን የሚያጥኑ አድርጓቸዋል። ራዕ፤ 4፣4 እነዚህ ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ የሚባሉት ሲሆን በቀንናበሌሊት ሳያቋርጡ ስብሐት ወክብር ለስሉስ ቅዱስ ይደሉ እያሉ ያመሰግኑታል። በእኛም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ምድራውያን ካህናት በሰማውያን ካህናት ምሳሌ “ስብሐት ወክብር ለስሉስ ቅዱስ ይደሉ …”  እያሉ ያመሰግኑታል። ይህንንም በኪዳን፣ በወንጌል በቅዳሴ ጊዜ ጥምጥማቸውን አውልቀው የሚያመሰግኑት በራዕይ 4፣10 በተጻፈው ምሳሌ ነው።

3ኛ. በኤረር ካሉት መላዕክት ሃያ አራት ሺህ መርጦ ለሰማይ አስራ ሁለት ሺህ ኆኅት /መስኮት/ አበጅቶ በእያንዳንዱ መስኮት ሁለት ሁለት መላዕክትን አስፍሯቸዋል። እነዚህ መላእክት ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በመብረር ዓለምን በሙሉ ይቆጣጠራሉ።

ከሰኞ ፍጥረት ምን እንማራለን ?

በእለተ እሑድ በፈጠረው ፍጥረት ምስጢረ ስላሴ እንደተገለጸ ሁሉ በዕለተ ሰኑይ ፍጥረት ምስጢረ ሥጋዌ ተገልጿል። ይህም ከምድር እስከ ብሩህ ሰማይ ኤረር ድረስ የሞላው ውሃ ከሶስት ከፍሎ ሁለት እጁን ማለትም ጠፈርንና ሐኖስን ከላይ ማስፈሩ፤ ሥጋ ለብሰው አልታዩምና የአብና የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው። አንዱ እጅ ወደ መሬት መውረዱ ከሶስቱ አካል አንዱ አካል ወልድ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት ወደ ምድር ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በተዋሕዶ ከብሮ የመወለዱ ምሳሌ ነው። “ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል አስተርአየ -   በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ” መዝ፤ 79፣1 የሚለው የቅዱስ ዳዊት ትንቢትና ልመና በወልደ እግዚአብሔር በምድር ላይ መገለጥ ተፈጽሟል።

በሚቀጥለው የዕለተ ረቡዕን ፍጥረታት እንመለከታለን። ይቆየን!

 

---------------------------------------------------------------------------------------------------------

ዓለም የተፈጠረችበት ዕለት መቼ ነው?

ዓለም የተፈጠረችው በዕለተ እሑድ፣ መጋቢት ሃያ ዘጠኝ ቀን፣ በዘመነ ዮሐንስ ነው። ዓለም ማለት በውስጡ ፍጥረታትን የያዘ የፍጥረታት መኖሪያ ማለት ነው። “በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ” ዘፍ፤ 1፣1 የሚለው ዓለም በዕለተ እሑድ የተፈጠረች መሆኑን ያሳየናል። ዓለም በዘመነ ዮሐንስ የተፈጠረች መሆኑ በምን ይታወቃል? በዚያን ጊዜ አራቱ  ወንጌላውያን አልነበሩም የሚለው ጥያቄ በአዕምሯችን መመላለሱ አይቀርም። እንደሚታወቀው ዘመናት በአራቱ ወንጌላውያን የተሰየሙ ናቸው። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሐዲስ ኪዳን የነበሩ ሊቃውንት አራቱ ወንጌላውያን የጌታን ቃል ለአራት ተካፍለው በተለያየ ቦታ፣ በተለያየ ዘመን፣ በተለያየ ቋንቋ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ስለጻፉት ለዚህ ውለታቸው ማለትም የድህነታችንን የምስራች ዜና ስላበሰሩን ዘመናትን ከፍሎ ለመታወቂያ አድርገዋቸዋል። ቅዱሳን ውለታ እንዲከፈላቸው የሚፈልጉ አይደሉም። ውለታ ክፈሉኝ ባይሉም እኛ ልጆቻቸው ግን ለፍቅራቸው መግለጫ ይሆን ዘንድ መታሰቢያ እናደርግላቸዋለን። እንዲህ ዓይነቱን ተግባር ደግሞ የተማርነው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለምሳሌ ዮሐንስ ወንጌላዊ እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ ተጉዞ ብቻውን በመገኘት ላሳየው ጥብአት ውለታ ይሆን ዘንድ እመቤታችን ድንግል ማርያም እናት ትሆነው ዘንድ በአደራ ተሰጥቶት ወደቤቱ ወስዷታል። ዮሐ፤ 19፣25 ፤ ኢሳ፤ 56፣4


ወንጌላውያኑ፣ ወንጌሉን የጻፉበት ቦታ፣ የጻፉበት ቋንቋ፣ የጻፉበት ዓመተ ምህረት የሚያሳይ ሰንጠረዥ፦

ተራ ቁ.
የወንጌላዊው ስም
 የተጻፈበት ቦታ
የተጻፈበት ዓመተ ምህረት
የተጻ/ ቋንቋ
  
   የዘመኑ ንጉስ
 1ኛ.
   ማቴዎስ
በፍልስጤም ጀምሮ
በህንድ ጨርሷል
ጌታ ባረገ ከ8 እስከ
   9ኛው ዓመት
ዕብራይስጥ
ቀላውዴዎስ ቄሳር በነገሰ በመጀመሪያው ዓመት
 2ኛ.
  
   ማርቆስ
በግብጽ ጀምሮ በሮም ጨርሷል
ጌታ ባረገ ከ11 እስከ
   12ኛው ዓመት
ሮማይስጥ
ቀላውዴዎስ ቄሳር በነገሰ በአራተኛው ዓመት
 3ኛ.
  
   ሉቃስ
   በመቄዶንያ
ጌታ ባረገ ከ21 -22ኛው ዓመት
ዮናኒ /ጽርዕ/
ቀላውዴዎስ ቄሳር በነገሰ በአስራ አራተኛው ዓመት
 4ኛ.
  
   ዮሐንስ
    በኤፌሶን
ጌታ ባረገ በ30ኛው  ዓመት
ዮናኒ /ጽርዕ/
  ኔሮን ቄሳር በነገሰ
 በስምንተኛው ዓመት


እነዚህ ወንጌላውያን በተለያየ ጊዜ ፣ በተለያየ ቋንቋ በተለያየ ቦታ ሆነው ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት አንዱን የእግዚአብሔርን ቃል የጻፉ ከመሆናቸው ባሻገር ስለ ዓመተ ምህረት ስንናገር ዓመተ ምህረት የሚለው ስያሜ የተገኘውና ዓመተ ፍዳ የሚለውን ዘመን የተካው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከዓመተ ፍዳ ወደ ዓመተ ምህረት፣ ከዓመተ ኩነኔ ወደ ዓመተ ጸድቅ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከቁራኝነት ወደ ልጅነት፣ ከባርነት ወደ ነጻነት የተሸጋገርነውም በእርሱ ነው። ይንን የነጻነታችንን ዜና፣ የምስራች ደግሞ ያገኘነው በደገኛይቱ ሕግ በወንጌል ነው።፡ወንጌል ማለት የምስራች ማለት ነው። የወንጌል ቃል በሙሉ የጌታችን ቃል ነው። ወንጌል ከመነበቡ በፊት “ዝ ቃል ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ከርስቶስ - ይህ ቃል የጌታችን የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ነው።” በማለት ካህኑ ያውጃሉ። በመቀጠልም በማን አማካኝነት እንደተጻፈ ማለትም ከአራቱ ወንጌላውያን ማን እንደጻፈው ይገልጻል። ይህ የሚያሳየው የጌታን ቃል ለእኛ በመጽሐፍ ጽፈው፣ በክርታስ ከርትሰው የሰጡን እነዚህ ወንጌላውያን መሆናቸውን ነው። ስለዚህ በዓመተ ምህረት ውስጥ የእነርሱ ድርሻ ታላቅ ስለሆነ ዘመናት በስማቸው ተሰይሞ ሲታወሱ እንዲኖሩ አባቶቻችን ወስነዋል። ለምድራውያን ባለስልጣናት፣ ታላላቅ ናቸው ብለን ለምናስባቸው እንኳን ስንት ሐውልት፣ ስንት መዘክር ይቆምላቸው አይደል?

ዘመኑ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ ወይም ዮሐንስ መሆኑ በምን ይታወቃል? ይህንን ለማወቅ ዓመተ ዓለሙን ማለትም ከጌታችን ልደት በፊት ያለውን ዘመን 5500ን እና ዓመተ ምህረቱን ማለትም ያለንበትን ዘመን በአንድ ላይ ደምረን ለአራት እናካፍለዋለን /በቁጥራቸው ልክ ማለት ነው። ካካፈልን በኋላ መጨረሻ ላይ የሚቀረው ቁጥር አንድ ከሆነ ዘመኑ ማቴዎስ፣ ቀሪው ሁለት ከሆነ ዘመኑ ማርቆስ፣ ሶስት ከሆነ ሉቃስ፣ ያለ ቀሪ ከተካፈለ ማለትም ቀሪው ዜሮ ከሆነ ዘመኑ ዮሐንስ ይሆናል። የወንጌላውያኑ ቅደም ተከተል ልክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳለው ነው። ይኸውም ከላይ በሰንጠረዡ እንዳየነው ወንጌሉን እንደጻፉት ቅደም ተከተል ማለት ነው።

ለምሳሌ አሁን ያለንበትን ዘመን ለማወቅ፦ ዓመተ ምህረቱ 2005 ነው። ይህንን ከዓመተ ዓለም ከ5500 ጋር እንደምረዋለን። ሁለቱ ሲደመር /5500 + 2005/ = 7505 ዓ.ዓ ይሆናል። ይህንን ለአራት ስናካፍለው /7505 ÷4/ = 1876 ጊዜ ደርሶ አንድ ይቀራል። ቀሪው አንድ ከሆነ ደግሞ ዘመኑ ማቴዎስ ይሆናል ማለት ነው። በየቤታችን የ2006፣ የ2007 እና የ2008ን በመስራት እንለማመድ። እንደ ቅደም ተከተላቸው መልሱን እናገኘዋለን።

ልክ እንደዚሁ ለአራት እያካፈልን ወደኋላ ስንመለስ ዓለም የተፈጠረችበት ዘመን ዘመነ ዮሐንስ መሆኑን እናገኘዋለን። ሌላው የሚነሳው ጥያቄ ቀኑስ መጋቢት 29 መሆኑ በምን ታወቀ የሚለው ነው። እንደሚታወቀው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጸነሰው በመጋቢት 29 ሲሆን የተወለደው ደገግሞ ታህሳስ 29 /ከዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በኋላ/ ነው። እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሲያበስራት ነው። “እንዘ ኢየዓርቅ እመንበረ ስብሐቲሁ ውስተ ማኅጸነ ድንግል ኀደረ ሥጋ ኮነ ወተወልደ - ከአባቱ አጠገብ፣ ከልዕልና መንበሩ ሳይለይ በድንግል ማኅጸን አደረ፣ ተወለደም” እንዲል ቅዱስ ያሬድ /መጽ፡ ዚቅ ዘልደት/። ይህ የሆነው መጋቢት ሃያ ዘጠኝ ቀን መልአኩ “ትጸንሲ ወትወልዲ ወልደ - ትጸንሻለሽ፣ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ” ሉቃስ፤ 1፣38 ብሎ ባበሰራት ጊዜ ነው። እንግዲህ ይህ ቀን ነገረ ድህነት የተጀመረበት፣ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን የተፈጸመበት ቀን ነው። በቤተ ክርስቲያን በዓለ ትስብእት በዓለ ድኅነት ይባላል። ምክንያቱም “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ - አምስት ቀን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው” /መጽ፡ ቀሌምንጦስ/ የሚለው ቃል የተፈጸመው በዚህ ቀን ስለሆነ ነው። ስለዚህ ልክ ዓለም በተፈጠረ፣ ዘመን በተቆጠረ 5500 ዓመት ሲፈጸም ጌታ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ተጸንሷል።

ስለዚህ ዓለም በተፈጠረበት ቀን ተጸንሷል ማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “ወአመ በጽሐ ዕድሜሁ ፈነወ አብ ወልዶ ወተወልደ እምብዕሲት - ዘመኑ ሲፈጸም እግዚአብሔር ከእመቤታችን የተወለደውን ልጁን ላከ” ገላ፤ 4፣4 ይላል። ይህም ማለት ቃል የገባበት ዘመን ሲፈጸም ከሰዓቱም፣ ከደቂቃውም አንዲት ሳይጎድል ወደዚህ ዓለም መጥቶ በድንግል ማርያም ማኅጸን አድሯል። አባቶቻችን “በደሃራዊ ልደቱ ለእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ተዓውቀ ቀዳሜ ልደታ ለምድር - በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛ  ልደት /ቀዳማዊ ልደቱ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ነው/ የምድር ቀዳማዊ ልደት ታወቀ” ይላሉ።  ይህም ቀን መጋቢት ሃያ ዘጠኝ ነው።   

ከእሑድ ፍጥረታት ምን እንማራለን?

እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ ስምንት ፍጥረታትን ፈጥሮ ያቆመው ደክሞት አይደለም። ይልቁንም በዚህ ቀን ምስጢረ ሥላሴን ሊያስተምረን ስለወደደ ነው። ከላይ አራቱ ባሕርያት እያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት ባሕርያት እንዳላቸው ተመልክተናል። ለምሳሌ እሳት ሶስት ባሕርያት / የሚያቃጥል፣ ብርሃንነት፣ክበብ /ደረቅነት - solid/ አለው። ነገር ግን ሶስት እሳት ወይም እሳቶች አንልም። ይልቁንም አንድ እሳት ነው የምንለው። እንደዚሁ ሁሉ እግዚአብሔር አምላክ የስም፣ የአካል የግብር ሶስትነት አለው። በዚህም ሥላሴ እንላለን። ነገር  ግን ሶስት እግዚአብሔር ወይም ሶስት አማልክት አንልም፤ ይለቁንም አንድ እግዚአብሐር፣ አንድ አምላክ እንላለን እንጂ። እራሱ ሥላሴ ማለት ሶስትነት ማለት እንጂ ሶስት ማለት አይደለም። ሶስት በምንልበት ጊዜ የየራሳቸው የሆነ ህልውና ባህርይ መልክ፣ ቅርጽ … ወዘተ አላቸው ማለት ነው። ሶስትነት ማለት ግን በአንድ ባሕርይ፣ በአንድ ህልውና ባለው ነገር ውስጥ ስለሚኖሩ ሶስት ነገሮች መናገር ነው። ውሃ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ሶስትነት /ሶስት ጠባያት/ አለው። ይኸውም እርጥብ ነው /ፈሳሽ ስለሆነ/፣ ብርሃናዊ ነው፣ እንዲሁም ቅዝቃዜ አለው። እነዚህ ሶስት ጠባያት ስላሉት ሶስት ውሃ አንለውም። እንዲሁም እግዚአብሔር የስም፣ የአካል የግብር ሶስትነት ስላለው ሶስቱ እግዚአብሔር አንለውም። ምክንያቱም በባሕርይ፣ በአነዋወር፣ በስልጣን፣ በመለኮት፣ በጌትነት /በመግዛት/ አንድ ስለሆነ ነው። 

ማስታወሻ

አራቱ ባሕርያት ከተፈጠሩ በኋላ የሰፈሩበት ቦታ፦

                                   እሳትን በኮሬብ፣                ውሃን በናጌብ፣
                                   ነፋስን በአዜብ፣                 አፈርን በዱዳሌም በሚባሉ ቦታዎች

 

---------------------------------------------------------------------------------------------------------

የእሑድ ፍጥረታት


እሑድ የሚለው አሐደ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን አንድ አደረገ ወይም የመጀመሪያ ማለት ነው። “ወበቀዳሚ እግዚአብሔር ገብረ ሰማየ ወምድረ - በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ።” ዘፍ፤ 1፣1 በዚህ ቀን እግዚአብሔር ስምንት ፍጥረታትን ፈጥሯል። በመጀመሪያው ሰዓተ ሌሊት /ከምሽቱ አንድ ሰዓት/ አምስት ፍጥረታትን የፈጠረ ሲሆን እነሱም እሳት፣ ውሃ፣ ነፋስ፣ መሬትና ጨለማ ናቸው።

እሳት፣ ውሃ፣ ነፋስና መሬት አራቱ ባሕርያት የሚባሉ ሲሆን በዓለም ውስጥ  ያሉ ሁሉም ፍጥረታት መገኛቸው እነዚህ ፍጥረታት ናቸው። አራቱ ባሕርያት እርስ በራሳቸው የማይስማሙ፤ አንዱ አንዱን የሚያጠፋ ሲሆን ነገር ግን እግዚአብሔር በረቂቅ ጥበቡ አስማምቷቸው ዓለምን ፈጥሮባቸዋል። እንዲሁም የአንዱ ፍጥረት ባሕርይ /ጠባይ/ በሌላው ውስጥ ስለሚገኝ ባሕርያቸው እርስ በራስ ይወራረሳል። ባሕርያቸው እንዴት እንደሚወራረስ ከዚህ ቀጥሎ እንመለከተዋለን።
1ኛ. እሳት፦ እሳት ሶስት ባሕርያት /ጠባያት/ አሉት እነሱም
·         ውዑይነት  /ሙቀትነት ወይም የሚያቃጥል/፣
·         ብሩሕነት  /ብርሃንነት/፣
·         ይቡስነት  /ደረቃማነት/ ናቸው።
እነዚህን ጠባያት ከሌሎች ባሕርያት የነሳው ሲሆን ይኸውም፦
·         ውዑይነትን /ሙቀትነትን / … ከነፋስ፣
·         ብሩሕነትን  /ብርሃንነትን/ …. ከውሃ፣
·         ይቡስነትን  /ደረቃማነትን/ … ከመሬት ነው።
2ኛ. ውሃ፦ ውሃም ሶስት ባሕርያት አሉት። እነዚህም፦
·         ብሩሕነት  /ብርሃንነት/፣
·         ርጡብነት  /እርጥብነት/፣
·         ቆሪርነት   /ቀዝቃዛነት/ ናቸው።
እነዚህን ባሕርያት ያገኘው ከሌሎቹ ሶስት ፍጥረታት ነው።
·         ብሩሕነትን … ከእሳት፣
·         ርጡብነትን … ከነፋስ፣
·         ቆሪርነትን    ከመሬት ነው።
3ኛ. ነፋስም በተመሳሳይ ሶስት ባሕርያት አሉት እነርሱም፦
·         ርጡብነት  …. እርጥብነት፣
·         ውዑይነት  …. ሞቃታነት፣
·         ጽሉምነት   …. ጨለማነት ናቸው።
እነዚህን ጠባያት የነሳው ወይም ያገኘው
·         ርጡብነትን  …. ከውሃ፣
·         ውዑይነትን  …. ከእሳት፣
·         ጽሉምነትን  …. ከመሬት ነው።
4ኛ. መሬት፦ መሬትም እንዲሁ ሶስት ጠባያት ሲኖሩት እነርሱም፦
·         ይቡስነት  …. ደረቃማነት፣
·         ጽሉምነት  …. ጨለማነት፣
·         ቆሪርነት   …. ቀዝቃዛነት ናቸው።
         እነዚህን ጠባያት የነሳው፦
·         ይቡስበትን  …. ከእሳት
·         ጽሉምነትን  …. ከነፋስ
·         ቆሪርነትን    …. ከውሃ ነው።
እነዚህ ፍጥረታት ከላይ እንደተገለጸው አንዱ ከአንዱ ጋር አይስማሙም፣ ይጣላሉ። ነገር ግን አንዱ ሌላውን እያስታረቀ በእግዚአብሔር ቸርነት ይኖራሉ። ለምሳሌ እንደሚታወቀው እሳትና ውሃ አይስማሙም፤ ውሃ አሳትን ያጠፋዋል። ነገር ግን ነፋስ ገብቶ ያስታርቃቸዋል። ነፋስና መሬት ጠበኞች ናቸው፤ ነፋስ መሬትን ይጠርገዋል፣ እንዲሁም ይሰነጥቀዋል። ነገር ግን ውሃ ገብቶ ያስታርቃቸዋል።
አራቱን ባሕርያት ለምን በመጀመሪያ ፈጠራቸው?
አራቱ ባሕርያት ቀድመው የተፈጠሩት አንድም ዓለም በሙሉ የሚፈጠረው ማለትም እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ /ካለምንም/ ከተፈጠሩት ውጪ ያሉት የሚፈጠሩት በእነዚህ ፍጥረታት ስለሆነ ከሌሎቹ ቀድመው ተፈጥረዋል። አንድም የእነዚህ ፍጥረታት እና የሌሎችም ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ በባሕርይው አራት ነገሮች እንዳሉት ለማጠየቅ ነው። እነዚህም ባዕልነት /ባለጸጋነት/፣ ርኅሩኅነት /ቸርነት/ ፣ ከሀሊነት /ሁሉን ቻይነት/፣ ፈታሒነት /ፈራጅነት/ ናቸው።
1ኛ. ባዕልነት በመሬት ይመሰላል፦
 ባዕልነት ማለት ባለጸጋነት ሲሆን ባለጸጋ ሁሉን ያስገኛል። እግዚአብሔር የሁሉ መገኛ እንደሆነ ሁሉ መሬትም የሚበላውን ፣ የሚጠጣውን … ወዘተ የምታፈራ፣ የምታስገኝ ናት። መዝ፤ 84 “እግዚአብሔር የሁሉ መገኛ ነው።’’ ይላል።
2ኛ. ርኅራኄውና ቸርነቱ በውሃ ይመሰላል፦
ውሃ ያደፈውን ያጠራል፣ የቆሸሸውን ያጸራል፤ ጌታም ኃጢአት ሰርተው ቢተዳደፉ ይቅር በለኝ ብለው በንስሃ ቢመለሱ ኃጢአትን ይቅር ይላል። ዮሐ፤ 6፣37
3ኛ. ከሃሊነቱ በእሳት ይመሰላል፦
እሳት ገደል፣ ባሕር፣ እውቂያኖስ ካልከለው በስተቀር ደረቁን፣ እርጥቡን ሁሉ ሳይለይ ያቃጥላል። እግዚአብሔርም ቸርነቱና ርኅራኄው ካልከለው በስተቀር ሁሉን ማጥፋት ይችላል። ዘፍ፤ 19፣1 ዘፍ፤7፣21 ማቴ፤19፣26 ሉቃ፤ 1፣37
4ኛ. ፈታሒነቱ በነፋስ ይመሰላል፦
ነፋስ ፍሬን ከገለባ ፣ ገለባን ከፍሬ እንደሚለይ ሁሉ እግዚአብሔር አምላክም ኃጥኡን ከጻድቁ፣ ምዕመኑን ከመናፍቁ ይለያል። ዘፍ፤ 7፣ 2 ማቴ፤ 3፣12 ማቴ፤ 25፣32
በዚሁ ሰዓት ማለትም በመጀመሪያው ሰዓተ ሌሊት አምስተኛውን ፍጥረት ጨለማን ፈጥሯል። “ምድር ባዶ ነበረች አንዳች አልነበረባትም ጨለማም በጥልቁ ነበረ።” ዘፍ፤ 1፣2
ከሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት እስከ ስምንተኛው ሰዓተ ሌሊት እግዚአብሔር ለፍጥረት ስድስተኛ የሆኑትን ሰባቱን ሰማያት ፈጥሯል። ሰማያት የተፈጠሩት ከእሳት ሲሆን ከእሳት ብርሃኑን ነስቶ /ወስዶ/ ሙቀቱን ትቶ ፈጥሯቸዋል። ሰባቱ ሰማያት የሚባሉትም፦
1ኛ. መንበረ መንግስት፦ ይህ ሰማይ በሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት የተፈጠረ ሲሆን በዚህ ቦታ እግዚአብሔር እንደወደደ ለቅዱሳኑ የሚታይበት ነው። ለምሳሌ ለያዕቆብ ዘፍጥ፤ 28፣12 ፤ ለነቢዩ ኢሳይያስ ኢሳ፤ 6፣1 ፤ ለነቢዩ ሕዝቅኤል ሕዝ፤ 1፣26 ፤ ለቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ራዕይ፤ 4፣2
2ኛ. ጽርሐ አርአም፦ ይህ ሰማይ በሶስተኛው ሰዓተ ሌሊት የተፈጠረ ሲሆን በመንበረ መንግስት ላይ ተዘርግቶ እንደ ጠፈር የሚጋርድ ነው። ሥላሴ በመንበራቸው ላይ ሆነው የሚሰለሱት፣ የሚቀደሱት በዚህ ሰማይ ነው። ሰባት የእሳት መጋረጃ ተጋርዶበታል ፣ሰባት የእሳት ቅጥር ተቀጥሮበታል። “ዘሰባቱ መንጦላዕት ዘእሳት አይቴ ተደለወ ወአይቴ ተተክለ - ሰባቱ የእሳት መጋረጃ በየት ተዘጋጀ? በየትስ ተተከለ?’’ ቅዳሴ ማርያም
3ኛ. ሰማየ ውዱድ፦ በአራተኛው ሰዓተ ሌሊት የተፈጠረ ሲሆን ይህ ሰማይ የሥላሴን ዙፋን የተሸከሙት አራቱ እንስሳት /ገጸ ሰብዕ ወይም የሰው መልክ ያለው፣ ገጸ አንበሳ፣ ገጸ ንስር ወይም ወፍ፣ ገጸ ላህም ወይም የላም መልክ ያላቸው/ ከነገደ ኪሩቤልና ከነገደ ሱራፌል የተወጣጡ መላእክት በእንስሳት መልክ ሆነው ዙፋኑን በጀርባቸው ተሸክመው የሚገኙበት ሰማይ ነው። ሕዝ፤ 1፣22 እና 26
4ኛ. ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፦ በአምስተኛው ሰዓተ ሌሊት የተፈጠረች ሰማይ ስትሆን ሳጥናኤል የተፈጠረው በዚህ ቦታ ነው። እርሱ ከወደቀ በኋላ ለሰው ልጆች ዘላለማዊ መኖሪያ እንድትሆን ተዘግታ የምትገኝ ናት። መንግስተ ሰማያት የምትባለው ይህቺው ሰማይ ናት። ዮሐ፤ 14፣1 የእመቤታችን ምሳሌ የሆነችው ታቦት ዘዶር የምትገኘው በዚህ ሰማይ ነው። ራዕይ፤ 11፣19   ቅዳሴ ማርያም
5ኛ. ሰማየ ኢዮር፦ በስድስተኛው ሰዓተ ሌሊት፣
6ኛ. ሰማየ ራማ፦ በሰባተኛው ሰዓተ ሌሊት፣
7ኛ. ሰማየ ኤረር፦ በስምንተኛው ሰዓተ ሌሊት ተፈጥረዋል። እነዚህ ሶስቱ ሰማያት ዓለመ መላዕክት ይባላሉ።
ከዘጠነኛው ሰዓተ ሌሊት ጀምሮ ለፍጥረት ሰባተኛ የሆኑት መላዕክት ተፈጥረዋል። እግዚአብሔር መላዕክትን ከፈጠረ በኋላ በሶስቱ ሰማያት ውስጥ በመቶ ነገድ፣ በአስር ከተሞች አስፍሯቸዋል። በአስሩ ከተሞች ውስጥ አስር የነገድ አለቆች ተሹመዋል። በዝርዘር ስናያቸው፦
በዘጠነኛው ሰዓተ ሌሊት ነገደ ሳጥናኤልን /አጋዕዝትን/፣ በአስረኛው ሰዓተ ሌሊት ነገደ ኪሩቤልና ነገደ ሱራፌልን፤ በአስራ አንደኛው ሰዓተ ሌሊት ነገደ ኃይላትን፣ በአስራ ሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት ነገደ አርባብን፣ ነገደ መናብርትንና ነገደ ሥልጣናትን፤ በአስራ ሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት  ነገደ መኳንንትን፣ ነገደ ሊቃናትንና ነገደ መላዕክትን ፈጥሯል።
መላዕክት ከሰፈሩበት ቦታ አይወጡም፣ አይናወጡም። ነገር ግን ለተልዕኮ ከላይ ከጽርሐ ዓርያም እስከ ታችኛው በርባሮስ ድረስ ይወጣሉ፣ ይወርዳሉ፣ ይላላካሉ። እግዚአብሔር መላእክትን ሲፈጥራቸው ጥበበኛና አስተዋይ አድርጎ ስለሆነ ፈጣሪያቸውን ተመራምረው ያግኙ! በማለት ከፈጠራቸው በኋላ ተሰወረ። በዚህን ጊዜ ሳጥናኤል ‘’እኔ አምላካችሁ ነኝ!’’በማለቱ ከስልጣኑ ወረደ። ሄኖ፤ 12፣3 የእርሱን ፈጣሪነት አምነው የተቀበሉት አብረው ሲወርዱ፤ በማመንና ባለማመን መካከል በመሆን የተጠራጠሩት ደግሞ በአየር ላይ የአየር አጋንንት ሆነው ቀርተዋል። በተቃራኒው የእርሱን አምላክነት ባለመቀበል በተሰጣቸው ጥበብ አማካኝነት አምላቸውን እሰኪያገኙ ድረስ በጽናት የታገሱት መላእክት ስለ እምነታቸው ጽናት፣ ስለትዕግስታቸው ብዛት ሹመትና ማዕረግ አግኝተዋል።
የዕለተ እሑድ የመጨረሻውና ስምንተኛው ፍጥረት ብርሃን ነው። “ለይኩን ብርሃን በማዕከለ ጽልመት - ብርሃን ይሁን አለ ብርሃንም ሆነ።” ብርሃንን በመጀመሪያው ሰዓተ መዓልት ወይም ከጠዋቱ በአንድ ሰዓት ፈጥሮታል። ይህ ብርሃን እውነተኛውን አምላካቸውን በትዕገስት በጠበቁ ቅዱሳን መላእክት ላይ ባበራ ጊዜ ብርሃኑ ዕውቀት ሆኗቸው እግዚአብሔርን ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ብለው አመስግነውታል። ኢሳ፤ 6፣1
በሁለተኛው ሰዓተ መዓልት መንፈስ ቅዱስ ክንፉን ዘርግቶ “የአብና የወልድ ሕይወታቸው እኔ ነኝ!” ብሎ ኅቡዕ ስሙ የተፃፈበት ሰሌዳ ሰጣቸው። እነርሱም ይህን ተቀብለው ስብሐት ለአብ፣ ስብሐት ለወልድ፣ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ብለው በማመስገን ሚስጥረ ሥላሌን መስክረዋል። ስለሃይማኖታቸው ጽናት፣ ስለትዕግስታቸው ብዛት አምላካቸው ሹሟቸዋል። ሹሞም የብርሃን ዘውድ አቀዳጃቸው፣ የብርሃን ዘንግ አስያዛቸው፣ የብርሃን አስኬማ ቀረጸባቸው። በዚህም መሰረት ከሶስተኛው ሰዓተ መዓልት እስከ አስራ ሁለተኛው ሰዓተ መዓልት ድረስ በአስሩ ከተሞች ውስጥ ያሉትን መላእክት በመሾም የየነገዱን አለቃ ሰይሞላቸዋል።
  የመላዕክት ከተሞች፣ ነገዳቸውና አለቆቻቸው በሰንጠረዥ፦

እንግዲህ እግዚአብሔር አምላክ እንደዚህ አድርጎ ሃያ አራቱን ሰዓት ስራ ሰርቶበታል። ይህም የሚያሳየው ሃያ አራት ሰዓት ስራ መስራት ተገቢ መሆኑንና የእርሱም ፈቃድ መሆኑን፤ አንድም በኋላ የሚነሱ ቅዱሳን አባቶች ሃያ አራት ሰዓት እርሱን ለማመስገናቸው ምሳሌ ነው። “እባርኮ ለእግዚአብሔር በኩሉ ጊዜ ወዘልፈ ስብሐቲሁ ውስተ አፉየ - እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ ምስጋናውም ዘወትር በአፌ ነው። መዝ፤ 33፣1
የጨለማና የብርሃን ምሳሌ፦
1ኛ. ካልፈለጋችሁኝ አታገኙኝም ሲል ጨለማን ፈጠረ። ብትሹኝ፣ ብትመረመሩኝ እገኛለሁ ሲል ብርሃንን ፈጠረ። ጨለማን በአርምሞ መፍጠሩ ሰሚ አካል /መላዕክት/ አልነበሩም። ብርሃንን በነቢብ /በመናገር/ ። “ለይኩን ብርሃን በማዕከለ ጽልመት - በጨለማ መካከል ብርሃን ይሁን” ማለቱ ሰማዕያን የሆኑ መላዕክት ስለተፈጠሩ ነው። “ብርሃኑን ቀን፣ ጨለማውን ሌሊት ብሎ ጠራው” ዘፍ፤ 1፣3 ሁለቱን አንድ አድርጎ ሃያ አራቱን ሰዓት አንድ ዕለት ብሎታል። ዘፍ፤ 1፣5 እና 13
2ኛ. ጨለማ የኦሪት፣ ብርሃን የወንጌል ምሳሌ ነው። “ሕዝብ ዘይነብር ውስተ ጽልመት ብርሃን ዐቢይ ሠረቀ ላዕሌሆሙ - በጨለማ ለሚኖሩ ሕዝቦች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው” ኢሳ፤ 9፣2 ፤ ሮሜ፤ 13፣12 በጨለማ ውስጥ ምንም አንደማይታይ ሁሉ በኦሪትም የሰው ልጅ ልጅነቱን ተገፎ በቀቢጸ ተስፋ ይኖር ነበር። በሐዲስ ኪዳን ጌታ ተወልዶ፣ ተጠምቆ፣ ሞቶ፣ ልጅነቱ ተመልሶ ብርሃን ሆኖለታል።
3ኛ. ብርሃንና ጨለማውን /ቀንና ሌሊቱን/ አንድ አድርጎ አንድ ቀን ማለቱ ኦሪትና ወንጌል ሕግ በመባል አንድ ለመሆናቸው ምሳሌ ነው። አንድም ጨለማ የትብስእት /የሥጋ/ ብርሃን የመለኮት ምሳሌ ነው። ሁለቱን አንድ አድርጎ አንድ ቀን ማድረጉ ሥጋና መለኮት በተዋሕዶ አንድ የመሆናቸው ምሳሌ ነው። ዮሐ፤ 1፣1
ይቆየን
-------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከየት ይጀምራል?


የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የሚጀምረው ከፍጥረተ ዓለም፣ ከፍጥረተ ጸሐይ፣ ከፍጥረተ ጨረቃ ጋር የተያያዘ ሲሆን የሚጀምረውም ጥንት ከሚለው ነው። ጥንትነቱም ከእነዚሁ ከዓለም፣ ከጸሀይ ፣ ከጨረቃና ከዋክብት መፈጠር ጋር የተያያዘ ሲሆን በጸሐይ ሶስት  ጥንታት አሉ። እነሱም፦-

1.      ጥንተ ዕለት፦ ጥንተ ዕለት እሑድ ሲሆን በዚህ ቀን ዓለም ማለትም ሰማይና ምድር የተፈጠረበት ቀን ነው።

2.     ጥንተ ቀመር፦ ይህ ዕለት ሠሉስ /ማክሰኞ/ ሲሆን በዚህ ቀን በዓለም ውስጥ የሚገኙ ፍጥረታት /ዕፅዋት፣ አዝርዕት፣ አታክልት/ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠሩበት ቀን ነው።

3.     ጥንተ ዮን፦ ጥንተ ዮን ዕለተ ረቡዕ ሲሆን በዚህም የቀንና የሌሊት መክፈያ የሆኑት ጸሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የተፈጠሩበት ቀን ነው። ዮን ማለት ጸሐይ ማለት ነው። “ዮን ይዕቲ ስማ ለጸሐይ ሀገረ ጸሐይ ዮን ይዕቲ” እንዲል።

እንግዲህ የኢትዮጵያ ዘመን መቆጠር የጀመረው ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ስለ ዘመን ቆጠራም ስንናገር “ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ” እንላለን። ስለዚህ ዘመን ቆጠራችን ከሥነ ፍጥረት ጋር የተያያዘ ነው።

ሥነ ፍጥረት ምን ማለት ነው?

ሥነ ፍጥረት ከሁለት ቃላት የተገኘ ሲሆን ሥን ማለት ያማረ፣ የሰመረ ማለት ሲሆን ፍጥረት ደግሞ የተፈጠረ ወይም የተገኘ ማለት ነው። ሥነ ፍጥረት ያማረ፣ የሰመረ የተዋበ ፍጥረት ማለት ነው።” ወርእየ እግዚአብሔር ኩሉ ዘገብረ ከመ ሠናይ ጥቀ - እግዚአብሔር ፍጥረታቱ ሁሉ መልካም እንደሆነ አየ’’ ዘፍ፤ 1፣21 ይላል። አንድም ሥነ ፍጥረት የፍጥረት መበጀት ወይም መሰራት ማለት ነው። የበጀ ማለት ደግም መልካም ማለት ነው። አንድም የፍጥረት መስማማት ማለት ነው። የማይስማሙና ጠበኞች የሆኑ አራቱ ባሕርያት በእግዚአብሔር ኃይል ተስማምተው ስለሚኖሩ የፍጥረት መስማማት እንለዋለን። /እንዴት ተስማምተው እንደሚኖሩ በሚቀጥለው ትምህርታችን እንመለከተዋለን/

የሥነ ፍጥረት አስገኚ ማን ነው?

በዚህ ዓለም ላይ ላሉ ነገሮች ሁሉ አስገኚ አላቸው። ለምሳሌ ሸክላ ያለሰሪ፣ ልብስ ያለ ሰፊ፣ ዕፅዋት፣ አታክልትና አዝርዕት ያለ መሬት፣ ሰው ያለእናት አባት እንደማይገኙ ሁሉ በዓለም ውስጥ ያሉ ፍጥረታት ሁሉ ያለፈጣሪ ሊገኙ አይችሉም። የሰማይ መዘርጋት፣ የምድር መርጋት፣ የቀንና የሌሊት፣ የበጋና የክረምት መፈራረቅ፤ እንዲሁም ነፋሳት፣ ደመናት፣ መባርቅት፣ ብርሃናት፣ ውሆች ሁሉ አዛዥና ገዥ፣ ፈጣሪ፣ አስገኚ እንዳላቸው ያሳያሉ።

ሥነ ፍጥረት ስንል አሁን እየተፈጠረ ያለ አዲስ ነገር አይደለም። ይልቁንም ከጥንት ጀምሮ በአባቶች ሲነገር የነበረ ነው። በአንዳንድ ሳይንቲስቶች አመለካከት በአሁን ሰዓት ሰው እያገኛቸው ያሉ ግኝቶችን ልክ አሁን እንደተገኙ ከዚህ ቀደም እንዳልነበሩ ተደርጎ ይነገራሉ። ነገር ግን ሁሉም ከጥንት ጀምሮ በአባቶቻችን በቃል ሲነገር፣ በጽሑፍ ሲሰፍር ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረ ነው። በአሁን ሰዓት የሰው ልጅ ጥቂቶቹን ተመራምሮ የደረሰባቸውን በማስተዋወቅ፣ በማስረዳት በስራ ላይ እንዲውሉ፣ ለአገልግሎት እንዲበቁ  አድርጓል። ይህ ማለት ግን ያልነበረውን አዲስ ፍጥረት ፈጥሯል ማለት አይደለም። ሥነ ፍጥረት አንድ ጊዜ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ “ሁሉም በእርሱ ሆነ/ተፈጠረ/፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” ዮሐ፤ 1፣3 እንዳለው።

እንደውም ለፈጣሪ መኖር ዋነኛው አስረጂዎች እነዚሁ ፍጥረታት ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ “ዓለማት በእግዚአብሔር ቃል እንደተዘጋጁ ስለዚህ የሚታየው ነገር ከሚታየው እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።” ዕብ፤ 11፣3 ይላል። እንዲሁም የማይታየውና ጥንት የማይታወቀው አምላክ በእነዚሁ በፍጥረታት አማካኝነት እንደተገኙም “ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም ተዐውቀ በፍጥረቱ በሀልዮ ወበአዕምሮ - የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሰሩት ታውቆ ግልጽ ሆነ።” ሮሜ፤ 1፣20 በማለት የማይታየው ፣የማይጨበጠው አምላክ መኖሩ የታወቀው በፈጠረው ፍጥረት ነው።፡ማር ይስሐቅም “ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘንተ ብከ ሰማዕት ወመምህር እምአፍአ ዘይመርኀከ ኀበ አእምሮተ እግዚአብሔር - የእግዚአብሔርን መኖር /ሕልውና/ ለማወቅ ከወደድክ መምህር ምስክር ሆኖ እግዚአብሐርን ወደማወቅ የሚመራህ ሥነ ፍጥረት አለልህ” /ማር ይስሐቅ እመጽሐፈ መነኮሳት ምዕ፤ 1 አንቀጽ 2/ ይላል። በእርግጥም አባቶቻን እግዚአብሔርን ፈልገው ያገኙት በፈጠረው ፍጥረት አማካኝነት ነው። ስርወ ሃይማኖት፣ አርከ እግዚአብሔር የተባለው አብርሃም በእግረ ልቡና፣ በፍኖተ አእምሮ ተጉዞ ከአምላኩ ጋር ያገናኙት እነዚሁ ፍጥረታት ናቸው። እኛ የምንኖርበትን ትንሽ ጎጆን ብንመለከት የቤቱን ጣራ ባለበት ቦታ ለማቆም ስንት ነገር ማለትም በዙሪያው የቆመው ግድግዳ፣ እርሱም ካልበቃው ቁጥራቸው እንደ ቤቱ ስፋት በሚወሰኑ ቋሚዎች /collens/ አማካኝነት ካልሆነ የቤቱ ጣራ ሊቆም አይችልም። ነገር ገን እግዚአብሔር የፈጠረውን ሰማይ ብንመለከት ይህን ያህል ከአድምስ እስከ አድማስ ሲዘረጋ መደገፊያ ግድግዳ ወይም ቋሚዎች አላስፈለጉትም። ቅዱስ ዳዊት “ሰማያት የእርሱን ጽድቅ /መኖር/ ይናገራሉ።” እንዳለው። መዝ፤ 18፣1 ፤ መዝ፤ 96፣6

እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ለምን ፈጠረ?

ከዓለማት አስቀድሞ እግዚአብሔር በአንድነት በሶስትነት /አንድነቱ ሶስትነቱን ሳይጠቀልለው፤ ሶስትነቱ ደግሞ አንድነቱን ሳይከፋፍለው/ ሲቀደስ፣ ሲሰለስ ይኖር ነበር። ባሕርይው ባሕርይውን እያመሰገነ በክብሩ በጌትነቱ ይኖር ነበረ። ዮሐ፤ 17፣5 ፤ ቅዳሴ ግሩም፤ ነገር ግን ክብሩ በራሱ ብቻ እንደቀረ ባየ ጊዜ ፍጥረታትን ልፍጠር ብሎ አሰበ። አስቦም አልቀረ ፍጥረታትን ፈጠረ። ምንና ምን ቢሉ፦

·         ሰውና መላእክትን ስሙን ለመቀደስ፣ ክብሩን ለመልበስ፣ መንግስቱን ለመውረስ፤

·         ሰማይና ምድርን ለፍጥረታት ማደርያ፤

·         አራቱን ባሕርያት /እሳት፣ ውሃ፣ ነፋስና መሬት/ ለፍጥረት መገኛ፤

·         ሌላውን ፍጥረት ለአንክሮ /እንዲደነቅበት/፣ ለተዘክሮ/ አምላክ መኖሩን ለማሳሰብ/ ለምግበ ሥጋ፣ ለምግበ ነፍስ ፈጥሯቸዋል። “ኩሉ ዘተፈጥረ ለመፍቅደ ነባብያን ቦ እምኔሆሙ ለምህሮ ወቦ እምኔሆሙ ለተገብሮ” እንዲል። ከላይ እንደተመለከትነው ለፈጣሪ መኖር ማረጋገጫ እንዲሆኑም ጭምር ፈጥሯቸዋል።

በዓለም ውስጥ ያሉ ፍጥረታት ስንት ናቸው?

እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት እያንዳንዱ ቢቆጠር ፍጡር ተናግሮ ባልጨረሰው ነበር። ይህን ያህላል ተብሎም በሰዎች አዕምሮም ሊወሰን አይችልም። ነገር ግን በየወገኑ፣ በየወገኑ፤ ብዙውን አንድ፣ ብዙውን አንድ አድርገን  ስንቆጥር ሃያ ሁለት ናቸው። “እስከ ሰባተኛይቱ ቀን ድረስ ሃያ ሁለት ፍጥረታትን ፈጠረ።” መጽ፡ ኩፋሌ፤ 3፣9 ይላል። ሊቀ ነቢያት ሙሴ የሥነ ፍጥረቱን ቁጥር የሃያ ሁለቱ አርእስተ አበው ምሳሌ አድርጎ ተናገሯል። እነዚህ አርዕስተ አበው ከአዳም ጀምሮ እስከ ያዕቆብ ድረስ ያሉ ናቸው። “ከአዳም ጀምሮ እስከ ያዕቆብ ድረስ ያሉ አበው ሃያ ሁለት ናቸው።” ኩፋ፤ 3፣9

እንዲሁም አዳም በገነት እያለ ይጸልይባቸው የነበሩ በኋላም ቅዱስ ዳዊት በመዘሙሩ ያነሳቸው ስመ አምላክ /የአምላክ ስሞች ሃያ ሁለት ናቸው። እነዚህም “አሌፍ፣ ቤት፣ ጋሜል፣ ዳሌጥ፣ ዋው፣ ዛይ፣ ሔት፣ ጤት፣ … ታው” መዝ፤ 118፣1 ያሉት ናቸው። ስለዚህ የሃያ ሁለቱ ፍጥረታት ቁጥር ከእነዚህ ጋር የተያያዘ ነው።    

 የሃያ ሁለቱ ሥነ ፍጥረት መገኛ

ፍጥረታት የተፈጠሩት በሁለት  መንገድ ሲሆን እነሱም፦

·         እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ - ከምንም ምን ወይም በባዶ፦ ካለምንም  የተፈጠሩ ሰባተት ፍጥረት ሲሆኑ እነሱም እሳት፣ ውሃ፣ ነፋስ፣ መሬት፣ ጨለማ፣ ሰባቱ ሰማያት እና መላዕክት ናቸው።

·         ግብር እምግብር ወይም ፍጥረት እምፍጥረት፦ እነዚህ ከአንድና ከዚያ በላይ ከሆኑ ፍጥረታት የተፈጠሩ ሲሆኑ ከላይ ከተጠቀሱት ሰባቱ ፍጥረታት ውጪ ሌላው አስራ አምስቱ በዚህ መልክ የተፈጠሩ ናቸው። መገኛቸውም ከአራቱ ባሕርያት /ከእሳት፣ ከውሃ፣ ከነፋስና ከሬት/ የተፈጠሩ ናቸው።  

ፍጥረታት ሲፈጠሩ በሶስት ዓይነት ሁኔታ ነው፦

·         በአርምሞ፦ በዝምታ ወይም ባለመናገር ሲሆን በአርምሞ የተፈጠሩ ሰባት ፍጥረታት ናቸው። እነሱም፦ አራቱ ባሕርያት፣ ጨለማ፣ ሰማያትና መላዕክት ናቸው።

·         በነቢብ /በመናገር/፦ በመናገር የተፈጠሩ አስራ አራት ፍጥረታት ሲሆኑ እነሱም ከብርሃን ጀምሮ ያሉ አስራ አራቱ ፍጥረታት ናቸው።

·         በገቢር / በመስራት /፦ በገቢር የተፈጠረው ሃያ ሁለተኛው ፍጥረት  አዳም ብቻ ሲሆን ከምድር አፈር አበጃጅቶ በሰባት ባሕርያት አጽንቶ ፈጥሮታል። ዘፍ፤ 2፣7 እነዚህ ሰባት ባሕርያት የሚባሉት አራቱ ባሕርያተ ሥጋ እሳት፣ ውሃ ፣ ነፋስና አፈር እንዲሁም ሶስቱ ባሕርያተ ነፍስ የሚባሉት ሕያውነት/ዘላለማዊነት/ ፣ ነባቢነት/ተናጋሪነት/ እና ለባዊነት/አስተዋይነት/ ናቸው።

በሚቀጥለው ከእሑድ እስከ ሰኞ የተፈጠሩትን ሃያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረታት እንመለከታለን። ይቆየን

4 comments:

 1. እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ሕይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 2. እባኮትን፡ይህን፡አብራርተው፡እንደጻፉት፡አምስቱ፡አዕማደ፡ሚስጥራትና፡ሰባቱ፡ሚስጥራተ፡ቤተክርስትያንን፡አብራርተው፡ይጻፉልን።በጉጉት፡እንጠብቃለን።

  ReplyDelete
  Replies
  1. ከዋከብትን ከሰው ልጅ ህይወት ጋ የሚያገናኘው ምንድን ነው;

   Delete
 3. የባህረ ሓሳብ ሶፍትዌር አንድ ወንድማችን ያዘጋጃት ይሄውላቹ ብሎናል http://eotc-mkidusan.org/site/images/stories/Bahire%20Hasab%202008%20setup.exe

  ReplyDelete

Thank you for your comments, we will response on timely manner.
thank you again.