Wednesday, September 26, 2012


ቅድመ ድሜጥሮስ ሕዝቡ በዓላትን እንዴት ያከብር ነበር?

እግዚአብሔር እምቅድመ ዓለም በልብ የመከረውን በነቢያት ያናገረውን ለመፈጸም በሥጋ ሰብዕ ተገልጿል/። በሥጋ ሰብዕም ተገልጾ ሕግ መጽሐፋዊ እና ሕግ ጠባይዓዊ ሲፈጽም አደገ። ሕግ መጽሐፋዊ ማለት በኦሪት እና በነቢያት ስለእርሱ የተጻፉትን እና የተነገሩትን መፈጸም ሲሆን ለምሳሌ።

·         በስምንት ቀን ቤተ ግዝረት ገብቶ መገዘር፣

·         በዐርባ ቀን ዕጉለ ርግብ ዘውገ መዕነቅ ይዞ ቤተ መቅደስ መግባት፣

·         በዓመት ሶስት ጊዜ ለገቢረ በዓል መውጣት “ለያስተርኢ ተባዕትከ ሠለስተ ጊዜያተ ለለዓመት” እንዲል፣

ሕግ ጠባይዓዊ ማለት በአንድ ሥጋ በለበሰ ሰው የሚንጸባረቁ ባሕርያት ሲሆኑ ለምሳሌ፦

·         በየጥቂቱ ማደግ “በበሕቅ ልሕቀ - በየጥቂቱ አደገ”

·         ለእናቱና ለቤተሰቦቹ መታዘዝ “እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ- ለቤተሰቦቹ እየታዘዘ አደገ” እንዲል።

Wednesday, September 19, 2012


ባሕረ ሐሳብን ማን ደረሰው?

ባሕረ ሐሳብን ለማወቅ ብዙ አባቶች ተመኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉ የሚሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና የመንበረ እስክንድርያ አስራ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ ለነበረው ለቅዱስ ድሜጥሮስ ተጸልጾለታል። ድሜጥሮስ ማለት መስታወት ማለት ነው። መስታወት፦ በጥርስ ያለውን እድፍ በጸጉር ያለውን ጉድፍ እንደሚያሳይ ሁሉ ድሜጥሮስም የተሰወሩ በዓላትን እና አጽዋማትን አሳይቶናል፤ አንድም ድሜጥሮስ ማለት መነጽር ማለት ነው። መነጽር፦ የራቀውን አቅርቦ የረቀቀውን አጉልቶ የተበተነውን ሰብስቦ እንደሚያሳየው ሁሉ ድሜጥሮስም የራቁ አዝማናትን አቅርቦ የተበተኑ አጽዋማትን ሰብስቧልና  መስታወት ተብሏል።

                                                ቅዱስ ድሜጥሮስ

Friday, September 14, 2012

የዘመን አቆጣጠር /ባሕረ ሐሳብ/


የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሐሳብ

መግቢያ

ኢትዮጵያ ሀገራችን የበርታ ቅርሶች ባለቤት መሆንዋን አይደለም እኛ ልጆችዋ ዓለም የሚመሰክረውና የሚያውቀው ሀቅ ነው። የራስዋ ብቻ ሀብት የሆኑ እጹብና ድንቅ የሆኑ ሀብት ባለቤት ናት። በተለይም ብቸኛ የሆኑት ፊደሎችዋ÷ አኩሪ የሆነው  የዘመን አቆጣጠርዋ÷ ልዩ የሆነው ባህልዋ ÷የቱሪስት መዳረሻ የሆኑት ቅርሶችዋ ÷በየትም ሀገር የሌለ የበርካታ ቋንቋዎች ማህደር መሆንዋና የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ። የእነዚህ በርካታ ሀብቶች ባለጸጋ ያደረገቻትና የበሬውን ድርሻ የምትወስደው ደግሞ የአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት።

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለሀገሪቱ ካበረከተችው በርካታ ሀብቶች መካከል ብቸኛ የሆነው የዘመን አቆጣጠርዋ ነው። ይህ የዘመን አቆጣጠር በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ባሕረ ሀሳብ ይባላል። የዚህ የባህረ ሐሳብ ትምህርት መገኛ የሆነው አቡሻሓር የተባለው ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው። ይህ ትምህርት ከአራቱ ጉባዔያት {ብሉይ ኪዳን÷ ሐዲስ ኪዳን ÷ መጽሐፈ ሊቃውንት ÷ መጽሐፈ መነኮሳት } ቀጥሎ የሚሰጥ የጥበብ ትምህርት ነው።

በዚህ ጽሁፍ የምንመለከተው የዚህ የአቡሻኻር ክፍል የሆነውን ባሕረ ሐሳብን /የዘመን አቆጣጠርን/ ይሆናል። በዚህ ትምህርት ውስጥ በዋናነት የምንዳስሰው፦

Tuesday, September 11, 2012

የዘመን አቆጣጠር

መስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም.
ባሕረ ሐሳብ ሶፍትዌርን ከዋናው ገጽ ዳውንሎድ አድርገው መጠቀም ይችላሉ
1. ባሕረ ሐሳብ ማለት ምን ማለት ነው?

ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽም የሐሳብ ባሕር ማለት ነው፡፡ በዓላት እና አጽዋማትን ለማውጣት የመደመር፣ የመቀነስ፣ የማባዛት ስሌትን ብቻ ሳይሆን ሐሳበ ፀሐይን፣ ሐሳበ ወርኅን፣ ሐሳበ ከዋክብትን ሐሳበ ዐበቅቴን ወዘተ አጠቃሎ የያዘ እንደ ባሕር የሰፋ በመሆኑ የሐሳብ ባሕር ተብሏል፡፡ የዘመን አቈጣጠር ማለት ስለማሕበራዊ ኑሮ ጠቄሜታና የሃይማኖት ተግባሮች ለማከናወን በሚያገለግል መልኩ ተፈጥሮአዊውን የወቅቶች ክፍፍል እርስ በርሳቸው የማመቻቸት ዘዴ ነው፡፡
ሐሳበ ዘመን የዘመን አቆጣጠር ማለት ሲሆን የሐሳበ ዘመን ትምህርት ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡ ባሕረ ሐሳብ የሚለው ቃል ሐሰበ ቆጠረ ከሚለው ግስ የወጣ ዘመድ ዘር ነው፡፡ ስለዚህ ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ወይም ዓመተ ዓለም ማለት ነው፡፡ ባሕረ ሐሳብ መባሉም የባሕር አዝዋሪቱ፣ መንገዱን፣ ጥልቀቱና ስፋቱ ረዥምና ሰፊ እንደሆነ የባሕረ ሐሳብ ትምህርትም መንገዱን ስፋቱ ልዩ ልዩ በሆነ የአጽዋማትና የሱባዔያት ምሥጢር የተሰናዳ ስለሆነ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር /የጊዜ ቀመር/ አንድ ዓመት በውስጡ ዐሥራ ሦስት ወራትን የያዘ ሆኖ በአራት ወቅቶች የተከፈለ ነው፡፡ አራቱ ክፍላተ ዘመን የሚባሉት፡- “ክረምት ከሰኔ 26 ቀን - መስከረም 25 ቀን፣ መፀው /መከር/ ከመስከረም 26 ቀን - ታኅሣሥ 25 ቀን፣ በጋ /ሐጋይ/ ከታኅሣሥ 26 ቀን - መጋቢት 25 ቀን፣ ጸደይ /በልግ/ ከመጋቢት 25 ቀን - ሰኔ 25 ቀን ናቸው፡፡ ከክረምት በስተቀር እያንዳንዱ ወቅት በውስጡ ዘጠና ዘጠና ቀናት ይዟል፡፡ ክረምት ግን ለብቻው 95 ቀናትን የያዘ ነው፡፡