Saturday, January 12, 2013

ወንበር

በዓላትንና አጽዋማትን ለማውጣት ከሚያስፈልጉን ነገሮች ውስጥ አንዱ መጥቅዕ ሲሆን በዓላትና አጽዋማት የሚያድሩባቸውን ሌሊት የሚያሳውቀን ደግሞ አበቅቴ ነው። አበቅቴና መጥቅዕ በየዘመኑ የሚቀያየሩ ስለሆነ ሁልጊዜ ማለትም በየዓመቱ የየዘመኑን አበቅቴና መጥቅዕ ማውጣት ይኖርብናል። እንግዲህ ወንበር እነዚህን አበቅቴንና መጥቅዕን የምናወጣበት ቁጥር ነው። ወንበር የሚለው ስያሜ የተገኘው አበቅቴም ሆነ መጥቅዕ /ለበዓላትና ለአጽዋማት መገኘት ወሳኙ የሆኑ ነገሮች/ የሚገኝበት ከመሆኑም በላይ ዓመቱን ሙሉ ቀሚ በመሆን የሚያገለግል ቁጥር ስለሆነ ነው።

ወንበር እንዴት ይወጣል?
ወንበርን በተለያየ መንገድ ማውጣት የምንችል ሲሆን ሊቃውንት አባቶቻችን እንደ ዛሬው የሂሳብ መቀመሪያ መሳሪያዎች ሳይኖሩ የሂሳብ ስሌቶችን የሚሰሩት በቃላቸው ነበር። አሁንም አብዛኛዎቹ በቃላቸው ነው የሚሰሩት። ለምሳሌ አንድን ትልቅ ቁጥር ለሆነ ቁጥር ማካፈል ቢፈልጉ /ለምሳሌ 7450ን ለ532 ለማካፈል/ የሚጠቀሙት እንደኛ ካልኩሌተር ሳይሆን በቃላቸው ነው የሚያካፍሉት። በዚህን ጊዜ ይንን ትልቅ ቁጥር ለማካፈል የተለያዩ መንገዶችነ ይጠቀማሉ። ስለዚህ ይህንን የአባቶችን ትውፊት መተው ተገቢ ስላልሆነ እንዲሁም አንዱም መንገድ በመሆኑ እንመለከተዋለን። ሌላው ደግሞ ዘመኑ የሰጠንን አጭር መንገዶችንም መጠቀሙ ለስራችን ቅልጥፍና የሚሰጠው በመሆኑ በዘመናዊ መንገድ በማለት እንመለከተዋለን።



ሀ. ወንበር በአበው ሊቃውንት ስሌት
እንደ አበው ሊቃውንትም ሆነ በአሁኑ ሰዓት በቀላሉ ለማውጣት በቅድሚያ ዓመተ ምህረትንና ዓመተ ፍዳን መደመራችንን መርሳት የለብንም። ዓመተ ፍዳ እንደሚታወቀው የሚለዋወጥ አይደለም፤ ሁልጊዜም ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን ዓመተ ምህረቱ በየዓመቱ እየጨመረ ስለሚሄድ ሁለቱ በአንድ ላይ መደመር አለባቸው። ተደምሮ የተገኘው ቁጥር ዓመተ ዓለም ወይም የዓለም ዕድሜ ይባላል። ይህንን ዓመተ ዓለም በዐቢይ ቀመር፣ በማእከላዊ ቀመር እና በንዑስ ቀመር በመግደፍ /በማካፈል/ የዘመኑን ወንበር እናገኛለን ማለት ነው።

ለምሳሌ፦ የ2005 ዓመተ ምህረትን ወንበር ለማግኘት በቅድሚያ ዓመተ ምህረቱን ከዓመተ ፍዳ ጋር እንደምራለን።
  ዓመተ ፍዳ  ሲደመር  ዓመተ ምህረት
   5500 + 2005 = 7505 /ሰባት ሺህ አምስት መቶ አምስት ዓመተ ዓለም/ ይሆናል።

አሁን ሊቃውንቱ ዓመተ ዓለሙን በየቤቱ ይከፍሉታል። የሺህ ቤቱን፣ የመቶ ቤቱን የአስር ቤቱንና የአንድ ቤቱ ለየብቻቸው ይቀመጣሉ። በዚህም መሰረት፦ 7000 ፣ 500 ፣ 5 ይሆናሉ።
የባለፈው ጽሁፍ ላይ እንደምታስታውሱት ከሰባቱ አዕዋዳት መካከል ሶስቱን ማለትም ዐቢይ ቀመርን፣ ማዕከላዊ ቀመርን እና ንዑስ ቀመርን በቃላችን እንድንይዛቸው ተነጋግረናል። እነዚህም ዐቢይ ቀመር 532 ፣ማዕከላዊ ቀመር 76፣ ንዑስ ቀመር 19 ናቸው። ከላይ በየቤቱ ያስቀመጥናቸውን ቁጥሮች እንደ ቅደም ተከተላቸው እናካፍላቸዋለን። ማለትም ሰባት ሺህን ለዐቢይ ቀመር /532/ ተካፍሎ የሚቀረውንና አምስት መቶን በመደመር ለማዕከላዊ ቀመር /76/፣ አሁንም ከዚህ የቀረውንና አምስትን በመደመር ለንዑስ ቀመር /19/ ማካፈል ነው።

7000 ÷ 532 = 13 ጊዜ ደርሶ 84 ይቀራል። ይህንን ቀሪ እና 500ን በመደመር ለማእከላዊ ቀመር እናካፍላለን።
 500 + 84 = 584


584 ÷ 76 = 7 ጊዜ ደርሶ 52 ይቀራል። ይህንን ቀሪ እና 5ን በመደመር ለንዑስ ቀመር ይካፈላል።
5 + 52 = 57
57 ÷ 19 = 3 ጊዜ ደርሶ ዜሮ ይቀራል። ይህ የሚቀረው ቁጥር ተረፈ ዘመን ይባላል። እዚህ ጋር አንድ አዋጅ አለን።

አዋጅ፦ “አሐደ አዕትት ለዘመን - ለዘመኑ አንድ ቀንስ”
ይህ ማለት ከቀሪው ላይ አንድ በመቀነስ ለዘመኑ ስጥ ማለት ሲሆን የዚህ ምክንያቱ ሊቃውንቱ እንደሚሉት “ስለተጀመረ ተቆጠረ ስላላለቀ ታተተ ወይም ተቀነሰ” በዓላትንና አጽዋማት የሚወጡት መስከረም አንድ ቀን ነው።  እንደትላንት ጳጉሜን አምስት ሆኖ በሚቀጥለው ቀን ዓመቱን መቁጠር እንጀምራለን። ለምሳሌ በዚህ ዓመት ጳጉሜን 5/2004 ብለን ውለን በማገስቱ ግን 2005 ብለናል። ስለዚህ ዓመቱ ስለተጀመረ 2005 ብለን ቆጥረናል። ዓመቱ ግን ገና ለ365 ቀናት ይቆያል። በመስከረም አንድ ላይ ሆነን የምናወጣቸው በዓላት እንኳን ከቆይታ በኋላ የሚከናወኑ ናቸው። ስለዚህ አባቶች እንዳሉት ዓመቱን ስለጀመርነው ቆጥረነዋል ነገር ግን ገና ስላላለቀ ማለትም ለማለቅ ብዙ ቀናት ስለሚፈጅ እዚህ ጋር አንድ እንቀንሳለን ማለት ነው።

በላይኛው ምሳሌ ላይ ቀሪው እንደ አጋጣሚ ሆኖ ዜሮ ሆኗል። ከዜሮ ላይ ደግሞ የሚቀነስ ነገር የለም። ይህንን በኋላ እንመለስበታለን። ለአሁኑ በሌላ ምሳሌ ነገሩን እናዳብረው።
ምሳሌ 2፦ የ2007ን ወንበር ለማውጣት በቅድሚያ ከዓመተ ፍዳ ጋር እንደምረዋለን።
5500 + 2007 = 7507 ይሆናል። ይህንን በየቤቱ እንከፋፍለዋለን። 7000፣ 500፣ 7 ይሆናል:፡


ሀ. 7000ን ለዐቢይ ቀመር /532/ እናካፍለዋለን። 13 ጊዜ ደርሶ 84 ይቀራል
ለ. 500ን እና 84 ደምረን ለማዕከላዊ ቀመር /76/ እናካፍለዋለን። 584 ለ 76 ሲካፈል 7 ጊዜ ደርሶ 52 ይቀራል።
ሐ. 7ን እና 52 ደምረን ለንዑስ ቀመር /19/ እናካፍለዋለን። 59 ለ 19 ሲካፈል 3 ጊዜ ደርሶ 2 ይቀራል።

እንግዲህ በአዋጃችን መሰረት ማለትም አሐደ አዕትት ለዘመን - አንዱን ለዘመኑ ስጥ በሚለው መሰረት ከቀሪው ላይ አንድ እንቀንሳለን። ቀሪው 2 ሲሆን አንስ ስንቀንስ አንድ ይቀራል። ስለዚህ በ2007 ዓ ዓመተ ምህረት አንድ ወንበር ወጣ ይባላል።
ወደ መጀመሪያው ምሳሌ እንሂድና ቀሪው ዜሮ ነው የሆነብን። ስለዚህ ቀሪው ዜሮ ከሆነ ደግሞ አንድ ስንቀንስ ዕዳ /negative/ ነው የሚሆነው። በዚህን ጊዜ ወንበር የለንም ማለት ነው። ይህ በየአስራዘጠኝ ዓመቱ አንድ ጊዜ የሚመጣ ሲሆን አንድ አውደ አበቅቴ /19 ዓመት/ ተፈጽሞ ሌላ አውደ አበቅቴ ሊጀምር ነው ማለት ነው። ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት አበቅቴው ዜሮ ይሆናል ማለት ነው። ምክንያቱም ስለ አዕዋዳት ስንማር አውደ አበቅቴ 19 ነው ብለናል። 19 የሆነውም ጸሐይና ጨረቃ በተፈጠሩበት መስኮት የሚገናኙበት ነው። አበቅቴ ደግሞ በፀሐይና ጨረቃ ዙረት ምክንያት የሚመጣ ልዩነት ነው። ምክንያቱም ፀሐይ የምትዞረው 365 ቀን ሲሆን የጨረቃ ዐውድ የሚያበቃው ደግሞ በ354 ቀን ነው በዚህ ዑደት መካከል ያለው ልዩነት 11 /አስራ አንድ/ ነው። ይህ አስራ አንድ የመጀመሪያው አበቅቴ ወይም ልዩነት ነው። ለዚህ ነው ድሜጥሮስ ከሌሊቱ 23 ሱባዔ በመግባት አስራ አንድ ጥንተ አበቅቴን ያገኘው።

ስለዚህ በ19 ዓመት አንድ ጊዜ ግን በአንድ መስኮት ስለሚገናኙ ያን ጊዜ አበቅቴ አይኖርም። አልቦ አበቅቴ ወይም ዜሮ ይሆናል ማለት ነው። ይህ ከሚሆንበት አንድ ዓመት ቀድሞ ደግሞ የአበቅቴ ፍጻሜ ይሆናል ማለት ነው። የአበቅቴ ፍጻሜ የሚሆነው ደግሞ ዘንድሮ /በ2005/ ነው። ለዚህ ነው ወንበሩ ከዜሮ ያነሰው። ዜሮ እንኳን አልሆነም ምክንያቱም ወንበር የምንለው ከተረፈ ዘመኑ ላይ አነድ ተቀንሶ ዜሮና ከዜሮ በላይ ሲሆን ነው። አሁን ግን ተረፈ ዘመኑ ራሱ ዜሮ ሆኗል። ከዜሮ ላይ ደግሞ አንድ ብንቀንስ ከዜሮ ያነሰ ወይም ኔጌቲቭ ነው የሚሆነው። ታዲያ በዚህ ጊዜ አበቅቴና መጥቅዕ እንዴት ይገኛል? የሚል ጥያቄ በአዕምሯችን መምጣቱ የማይቀር ነው። ምክንያቱም የወንበር ጥቅም አበቅቴና መጥቅዕን ማስገኘት እንደ ሆነ መግቢያችን ላይ አስቀምጠናል። ይህንን ስለ አበቅቴ ስንማር እንመለስበታለን። ይቆየን!        

4 comments:

  1. This is wonderful mathematical science that we all the holders don't know. Why we skipped such basis while we suppose to study science?

    ReplyDelete
    Replies
    1. Whenever technology achievements in the 20th century impress me, same question cross my thoughts and my quick conclusions? 'We have been fighting each other constantly' and , worse, the church that have the knowledge riches did not want to be influential to the society in a scientific way. During the same period, western Christians have been preaching around the world including Ethiopia, equipped with both the Bible and their personal philosophy and offering political strategies to the kings. The past is gone, right? Now, see the trend and evaluate what we are doing, and ensure not to lag behind again. Yet still it is the western that say the current binary computer system uses similar method to the basic but ingenious of an ancient Ethiopian routine math method: http://www.youtube.com/watch?v=uXOTKidm7A0
      So, yes, we have skipped a lot!

      Delete
  2. This comment has been removed by a blog administrator.

    ReplyDelete

Thank you for your comments, we will response on timely manner.
thank you again.