Friday, September 14, 2012

የዘመን አቆጣጠር /ባሕረ ሐሳብ/


የኢትዮጵያ ታላቁ ሀብት ባሕረ ሐሳብ

መግቢያ

ኢትዮጵያ ሀገራችን የበርታ ቅርሶች ባለቤት መሆንዋን አይደለም እኛ ልጆችዋ ዓለም የሚመሰክረውና የሚያውቀው ሀቅ ነው። የራስዋ ብቻ ሀብት የሆኑ እጹብና ድንቅ የሆኑ ሀብት ባለቤት ናት። በተለይም ብቸኛ የሆኑት ፊደሎችዋ÷ አኩሪ የሆነው  የዘመን አቆጣጠርዋ÷ ልዩ የሆነው ባህልዋ ÷የቱሪስት መዳረሻ የሆኑት ቅርሶችዋ ÷በየትም ሀገር የሌለ የበርካታ ቋንቋዎች ማህደር መሆንዋና የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ። የእነዚህ በርካታ ሀብቶች ባለጸጋ ያደረገቻትና የበሬውን ድርሻ የምትወስደው ደግሞ የአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት።

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለሀገሪቱ ካበረከተችው በርካታ ሀብቶች መካከል ብቸኛ የሆነው የዘመን አቆጣጠርዋ ነው። ይህ የዘመን አቆጣጠር በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ባሕረ ሀሳብ ይባላል። የዚህ የባህረ ሐሳብ ትምህርት መገኛ የሆነው አቡሻሓር የተባለው ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው። ይህ ትምህርት ከአራቱ ጉባዔያት {ብሉይ ኪዳን÷ ሐዲስ ኪዳን ÷ መጽሐፈ ሊቃውንት ÷ መጽሐፈ መነኮሳት } ቀጥሎ የሚሰጥ የጥበብ ትምህርት ነው።

በዚህ ጽሁፍ የምንመለከተው የዚህ የአቡሻኻር ክፍል የሆነውን ባሕረ ሐሳብን /የዘመን አቆጣጠርን/ ይሆናል። በዚህ ትምህርት ውስጥ በዋናነት የምንዳስሰው፦


·         የበዓላትና የአጽዋማትን ቀመር

·         የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እና ሌሎች በዓለም ዙሪያ ያሉ አቆጣጠሮች ለዩነት

·         የዓለም ወይም የዘመን ፍጻሜ የባሕረ ሓሳብ ሊቃውንት ምልከታ

·         የተረሱን ወይም የጠፉንን ቀናት እንዴት ማግኘት እንደምንችል እና ተያያዥ ጉጋዮችን ለመዳሰስ እንሞክራለን



እኛ ኢትዮጵያውያን የዚህ እና የሌሎች ድንቅ ሀብቶች ባለቤት ብንሆንም ከመጠቀሚያነት በዘለለ ከየት እንደመጣ እና ምክንያቱን ለማወቅ ብዙም አያስጨንቀንም። ይልቁንም የእኛን ታሪክ አውሮፓውያን ሲያጠኑና ሲመራመሩ እንመለከታለን። አልፎም የእኛን ሀብት ሌሎች በባለቤትነት ይዘውትም ተመልክተናል። ለምሳሌ የግዕዝ ቋንቋ የኢትዮጵያ ቋንቋ ለመሆኑ ምስክር መቁጠር የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ በአሁን ሰዓት አንዲት አውሮፓዊት ሀገር የእኔ ነው ማለት ጀምራለች። ምክንያቱም ቋንቋውን በሀገሯ ላይ ብዙ ምርምሮችን በማድረግና በታላላቅ ዩኒቨረሲቲ ውስጥ በማስተማር በርካታ ዜጎች ያውቁታል÷ በሚገባ መናገር ጀምረዋል። የእኛ ቋንቋ የነበረው ባለቤትነቱ የእኛ ነው ስላላልን አይናችን እያየ ተቀምተናል። የአባቶቻችን ተረት “ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል” የሚሉት እንዲህ ዓይነቱን ነው። በሀገራችን የትኛው ትምህርት ቤት ወይስ የትኛው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው የግዕዝ ትምህርት የሚሰጠው?

በተመሳሳይ የዘመን አቆጣጠራችን እጅግ አስደነቂና የቀድሞ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ደርሰውበት የነበረውን የስልጣኔ ደረጃ በሚገባ የሚያሳየንና በእርግጥም ቤተ ክርስቲያናችን የስልጣኔ ፈር ቀዳጅ መሆኗን በሚገባ የሚያሳይ ነው። ይሁን እንጂ ልክ እንደ ግዕዙ ሁሉ ባለቤት የሌለው ይመስል አቆጣጠሩ ከሌላ እንደመጣ ሲነገር ሰምተናል። በ2000 ዓ.ም /በሚሊኒየሙ / በዓል ሲከበር አንድ ሚኒስትር ይንኑ ማለትም የኢቶጵያ ዘመን አቆጣጠር የጁሊየስ ቄሳር መሆኑን አውጀዋል። አንድ ባለቅኔ ስለኢትዮጵያውያን ሲቀኝ ‘’ኢትዮጵያውያን በወርቅ ላይ ተኝተው ወርቅ ይለምናሉ’’ ብሏል። ይህ የሚየሳየው እኛ እራሳችን ለራሳችን የምንሰጠ አናሳ ግምት መሆኑን ነው። የዚህ ግንዛቤ ምክንየቱ ደግሞ ለታሪካችን ደንታ ቢስ በመሆናችን እና ስለማናውቅም ነው። ስለዚህ የራሳችን አንጡራ ሀብት የሆኑ ታሪኮቻችን አሳልፈን እንሰጣለን አልያም ስንነጠቅ ቆመን በዝምታ እንመለከታለን።


እንዲህ ዓይነቱ የተሳሳተ ግንዛቤ የሚወገደው ደግሞ ታሪካችንን በሚገባ በማወቅ ነው። ለዚህ ነው ከታሪኮቻችን እና ከልዩ ሀብቶቻችን መካከል አንዱና ትልቁ የሆነውን ባሕረ ሐሳብ በዚህ መድረክ ላይ ማቅረብ ያስፈለገው። የቅዱሳን አምላክ እገዚአብሔር ፈቃዱ ቢሆንና የእመቤታችን የድንግል ማርያም አማላጅንት ከእኛ ጋር ሆኖ ባሕረ ሓሳብን እየተማርን እግረ መንገዳችንን የሀገራችንን ታሪክ የአባቶቻችንን ጥበበኝነት እንመለከታለን። መልካም ጊዜ ይሁንልን።

ባሕረ ሐሳብ                                      

ባሕረ ሐሳብ ከሁለት የግስ ቃል የተገኘ ሲሆን ይኸውም ባሕር እና ሓሳብ ይባላሉ። ባሕር  ማለት ዘመን ማለት ሲሆን በሁለት ምክንያቶች ባሕር  ዘመን ተብሏል። ባሕርን ዘመን ሲለው "በመዳልው ደለወ ዓለመ ወበመስፈርት ሰፈራ ለባሕር”  ይላል። ይኸውም ባሕር ምንም ያህል ሰፊ ቢሆንም ጊዜ ይወስዳል እንጂ ልስፈረው ብሎ የተነሳ ሰው ይሰፍረዋል። እንዲሁም ሁሉ ዘመን እጅግ ብዙ እና ሰፊ ነው። ይሁን እንጂ በአዕዋዳት ይታወዳል በቀመር ይቀመራል። ስለዚህ ዘመንን ባሕር ይለዋል። ሌላው ባሕር እጅግ ሰፊና ምጡቅ የሆነ ነገር ነው ። ባሕረ ሀሳብም በውስጡ እጅግ ሰፊ የሆነና ምጡቅ የሆነ ትምህርትና እውቀት ያየዘ ነው።  ስለዚህ ዘመን ባሕር ተብሏል።

ሐሳብ ማለት ደግሞ ቁጥር ማለት ነው። ሐሳብን ቁጥር ሲለው ‘’ኢትትሀሰብዎሙ ወርቆሙ ወብሩሮሙ ወለጽድቅከኒ አልቦቱ ሐሳብ--  ለጽድቅህ ቁጥር የለውም’’ ማለት ነው። እንዲሁም “ብጹዓን እለ ተሓድገ ሎሙ ሓጢዓቶሙ ወእለ ኢሓሰበ ሎሙ ኩሉ ጌጋዮሙ -- ሓጢአቱ ያልተቆጠረበት ሰው ምስጉን ነው” ይላል። በአንድ ላይ ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጠር ያለው ዘመን ማለት ነው። አንድም ሐሳበ ዘመንም ይባላል ይኸውም የዘመን ቁጥር ማለት ነው።

ባሕረ ሐሳብን ማን ሊማረው ይገባል?

ባሕረ ሐሳብን ሁሉም ሰው ሊማረው ይገባል። በተለይም ካህናት  የመማር ግዴታ አለባቸው። እንደውም ባሕረ ሐሳብን ያልተማረና የማየውቅ ካህን በደረቅ ወንዝ እንደሚመሰል አባቶች ያተምራሉ። ባሕረ ሐሳብን የማያውቅ ካህን በደረቅ ወንዝ እንደሚመሰል ለማሳየት፦ “ካህን ዘኢየዓምር ሐሳበ ባሕር ይመስል ከመ ፈለግ ዘአልቦ ማይ ውስቴቱ--ባሕረ ሐሳብን የማየውቅ ካህን ደረቅ ወንዝን ይመስላል” እንዲል፤ ለምን ቢሉ ነጋድያን/ በእግራቸው ሄደው የሚነግዱ / ከሩቅ ሆነው ወንዝ ባዩ ጊዜ ተደስተው “ወደ ወንዙ ሄደን ጥቂት አርፈን ጥሬ ቆርጥመን ጠል ነስትን ውሃ ተጎንጭተን እንነሳ” ብለው ይሄዳሉ ወንዙ ጋር ደርሰው ውሃ ሲያጡበት አፍረውና ተሳቀው ይመለሳሉ። እንደዚሁም ሁሉ ምዕመናን ካህንን በሩቅ ሆነው ጠምጥሞ አምሞ ሲያዩት ወደ እርሱ ሄደው በዓላትን አውጥቶ አጽዋማትን ለይቶ እዲነግራቸው በጠየቁት ጊዜ ሞያ ባጡበት ጊዜ አፍረውና ተሳቀው ይመለሳሉ። ስለዚህ ካህን በዓላትን አውጥቶ አጽዋማትን ለይቶ ለመናገርና ለምዕመናን ለማሰተማር ይችል ዘንድ ባሕረ ሐሳብን ሊማር ይገባዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ቀን ሌሊቱ የየራሱ የሆነ ቁጥር አለው። ማለትም ዛሬ ቀኑ ይሄን ያህል ነው ስንል ለምሳሌ ዛሬ መስከረም አንድ ነው ስንል ይህ አቆጣጠር በጸሀይ ዑደት /ዙረት/ የሚገኝ ነው። ነገር በዚህን ቀን ያደረው ሌሊቱ ከቀኑ ጋር እኩል አይደለም:፡ ምክንያቱም የሌሊቱ አቆጣጠር የሚገኘው በጨረቃ ዑደት ነው። ስለዚህ ሌሊቱ የሚገኘው ዕለቱ ከአበቅቴና ከሕጸጽ ጋር ተደምሮ ነው። /ይህንን ወደፊቱ በስፋት የምናየው ይሆናል/ ስለዚህ ካህኑ ጸሎት ሲያደርግ /ሲያሰርቅ/ ዕለቱን ፣ ሌሊቱን እና ጨረቃውን በማንሳት ማስረቅ ይኖርበታል፤ ለዚህ ደግሞ ባሕረ ሐሳብ ማወቅ ይኖርበታል።  

እንዲሁም ምዕመናን ባሕረ ሓሳብን ሊማሩና ሊያውቁ ይገባል። ምክንያቱም ምዕመናን የሚያንሱበት ዓላውያን የሚበዙበት ዘመን ይመጣል። አልፎም በስደት ወደ ባዕድ ሀገር መሄድ ይኖራል። በዚህን ጊዜ በዓላትን አውጥቶ አጽዋምትን ለይቶ የሚነግር ካህን ማግኘት አይቻልም። በዚህን ጊዜ በዓላትን አውጥቶ ለማክበር አጽዋማትን ለይቶ ለመጾም ይቻል ዘንድ እያንዳንዱ ምዕመን ባሕረ ሀሳብን ማወቅ ይኖርበታል ፤ እንዲያውቅም ይመከራል።

በተጨማሪም ባሕረ ሐሳብን ስንመለከተው ከምንጠብቀው በላይ የሚያስደስትና ቤተ ክርስቲያኒቱንም ሆነ ሀገራችንን የሚያኮራ የጥበብ ትምህርት ነው። ይህንን በሂደት ከሚከተሉት ተከታታይ ጽሁፎች የምንመለከተው ይሆናል። የራሱ የሆነ ቀመር ያለው ፤ እንዲሁም የአበው ሊቃውንት ስሌት በዘመናዊ የሂሳብ ስሌት እተቀየረ እና እየተሰራ አሁንም ጭምር በማደግ ላይ ነው። አንድ ነገር በሂደት /in process/ ውስጥ ካለ ዘመናዊ /modern/ የመሆኑ መገለጫ ነው። ስለዚህ ይህንን የቤተ ክርስቲያን ሀብት እና የሀገር ኩራት የሆነውን ትምህርት ወጣቱ ትውልድ ተምሮና አውቆ ለሌላው በማስተማር ለተተኪ ትውልድ የማስተላለፍ ሓላፊነትና ግዴታ አለበት። በሚቀጥለው ባሕረ ሐሳብን ማን እንደደረሰው እንመለከታለን።  


                                                                                               

8 comments:

  1. This is very nice lessor for all Ethiopians, please keep this going.
    May God be with your work
    Megabi Tebebe

    ReplyDelete
  2. This is very nice and encouraging indeed.But, I suggest if you include reference lists(bibliographic sources)that will help to do more research and it also increase the credibility of your piece of work.

    ReplyDelete
  3. በጣም ጥሩ ጦማር ነው እግዜር ይስጥልኝ

    ReplyDelete
  4. I am v ery excited to learn Bahire Hasab and Geez if possible

    ReplyDelete
  5. bettam des ymeil new yeketel

    ReplyDelete
  6. Also se "The Ethiopic Calendar" by Dr. Aberra Molla (1994)

    http://ethiopiancalendar.wordpress.com/history/

    ReplyDelete
  7. ለትምህርቱ አግዚአብሔር ይስጥልን፣ ሊያሳዩን የፈለጉት ሰንጠረዥ በባእድ ቋንቋ የተጻፈ አንደሆነ ተመልክቼአልሁ፣ ሌላው፥ አማርኛውን በበለጠ ለመግለጽ ወደ አንግሊዝኛ ተርጉመውታልእና፤ ሌሎች ኣውሮፓውያን ነጠቁን የምንለውን ያህል አኛው አራሳችን እየቆነጣጠብን እየሰጠን እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን። ብዙዎቻችን ተሰርተው የተቀመጡ የሰው (የአውሮፓውያንን)ምስል አንስቶ መለጥፍ ይቀለናል ሆኖም፥ ከምንናገረውና ከውጥናችን ጋር አንዳይጋጭ አደራ። ትምህርቱ ለመከታተል ዝግጁ ነኝ፡

    ReplyDelete
  8. I agree with the comment by Temesgen. This is a very nice article except that it lacks references and sources. See a 1994 article link below from where the Enoch Calendar picture here came from.
    http://archive.today/hKHz

    ReplyDelete

Thank you for your comments, we will response on timely manner.
thank you again.